የወልዲያ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታዲየም እና የስፖርት ማዕከል ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ዛሬ ተመርቋል ።
በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሰለኝን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
የወልዲያ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታዲየም እና የስፖርት ማዕከል የስፖርት ዕድገት ላይ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የስታዲየሙ እና የስፖርት ማዕከሉ ግንባታ ባጠቃላይ ከ567 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን፥ ሙሉ በሙሉ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ወጪው ተሸፍኗል።
በወንበር ከ25 ሺህ 600 በላይ ተመልካቾችን ማስተናገድ የሚችለው ስታዲየሙ፤ 10 የመግቢያ በሮች አሉት።
ከአስሩ የመግቢያ በሮች ስድስቱ ተመልካቾችን የሚያስገቡ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ የክብር እንግዶች፣ የተጫዋቾች እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች መግቢያ መሆናቸው ታውቋል።
የስታዲየሙ በሮች በአካባቢው ባሉ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ቦታዎች እንደዚሁም ስታዲየሙ እንዲገነባ ትልቅ ሚና በተጫወቱ ሰዎች ስም ነው የተሰየሙት።
የወልዲያ ስታዲየም በኢትዮጵያ ታሪክ ሙሉ በሙሉ ጣሪያ ያለው በመሆን የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
የዓለም አቀፍ አትሌቲክሶች ማህበር ደረጃን ያሟላ ባለ ስምንት መም የመሮጫ ትራክ፣ የአሎምፒክ ውድድርን የማስተናገድ አቅም ያለው መዋኛ ገንዳ፣ የቅርጫት ኳስ ሜዳ፣ የእጅ ኳስ፣ የመረብ ኳስና የቴንስ መጫዋቻዎችን ያካተተው የወልዲያ ስታዲየም ግንባታው አራት ዓመት ተኩል ወስዷል።
ከአካባቢው ማህበረሰብ በተሰበሰበ 31 ሚሊየን ብር የተገነቡ የእንግዳ ማረፊያዎችም አሉት።
የአካበቢው ማህብረሰብ የስታዲየሙን ምርቃት አስመልክቶ ከትናንት ጀምሮ ደስታውን እየገለፀ ሲሆን፤ ሙሉ በሙሉ ገንብቶ ለሰጣቸው ለሚድሮክ ኢትዮጵያ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ከዚህ በፊት የስፖርት ማዘውተሪያዎች በበቂ ሁኔታ ባለመኖራቸው፤ የዞኑ የተለያዩ የስፖርት እንቅስቃሴዎች ተቀዛቅዘው የነበረ ሲሆን፤ የስታዲየሙ መገንባት ለአካበቢው ማህበረሰብ ትልቅ የሆነ የስፖርት መነቃቃትን እንደሚፈጥር ነዋሪዎቹ ገልጸዋል (ኤፍ.ቢ.ሲ) ።