ኮሚሽኑ  በጃንሜዳ ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያና ፍርድ ቤት አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታወቀ

በጃንሜዳ ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያና ፍርድ ቤት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ ፡፡

ኮሚሽኑ የከተራና ጥምቀት በዓላት አከባበር አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ፤በአዲስ አበባ ከተማ በታቦት ማደሪያ ስፍራዎች በተለይም በርካታ የበዓሉ ታዳሚዎች በሚገኙበት ጃንሜዳ ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያና ፍርድ ቤት በመክፈት አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቷል ።

ምእመናኑ በጸበል መርጨት ስነ ስርዓት ወቅት በሚፈጠር ግፊያ ጉዳት እንዳይደርስበትና ንብረቱ እንዳይሰረቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ  ነው ያመለከተው ።

የዕምነቱ ተከታዮችበዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ  ከጸጥታ ኃይሎች የተለመደውን ትብብር እንዲያደርጉ ኮሚሽኑ ጠይቋል ፡፡

የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት ታቦት በሚያልፍበት ወቅት የትራፊክ ፖሊስ አባላት ለሚሰጡት ትዕዛዝ ህብረተሰቡና አሽከርካሪዎች የተለመደ ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳሰቧል ።

በዓሉ እስኪጠናቀቅ ድረስም በጃንሜዳ ዙሪያ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ ክልክል በመሆኑ አማራጭ ቦታዎች እንዲጠቀሙ ነው ኮሚሽኑ ያመለከተው ።

ኮሚሽኑ ለጥምቀት በዓል የተለመደ አስፈላጊውን ዝግጅት በማጠናቀቁ ህብረተሰቡ ለጸጥታ ማስከበሩ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው ጥሪ ያስተላለፈው ።

ህብረተሰቡ የወንጀል ድርጊቶችን ሲመለከት በ011-126-43-77፣ 011-126-43-59፣ 011-827-41-51 ፣ 011-111-01-11 እና በ991 ነፃ የስልክ መስመር ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡