ፓትርያርኩ ሰላም ሊጎለብት የሚገባው መልካም እሴት መሆኑን አስገነዘቡ

የሀገራችን ሰላም ሊጎለብት የሚገባው መልካም እሴት መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ  አቡነ ማትያስ አስገነዘቡ ።

በአዲስ አበባ ትናንት የከተራ በዓል ሲከበር ፓትሪያሪኩ ለምእመናኑ እንዳስገነዘቡት በዓሉ በእምነቱ ተከታዮችና ጎብኚዎች ዘንድ ተከብሮ ሊውል የቻለው በሀገሪቱ በሰፈነው ሰላም ምክንያት ነው  ፡፡

ስለሆነም የሀገራችን ሰላም እንዲጎለብት ህዝቡ በፍቅር በአንድነት ተጠብቆ እንዲኖር

ሁሉም በጋራ ሊረባረብ እንደሚገባ አስረድተዋል ፡፡

ይኸው ማኅበራዊ እሴት የሆነው ሰላም በጥምቀት ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላት ላይ መከናወን እንዳለበትም አመልክተዋል ፡፡

ሰላም ከሁሉም በላይ ነው፤ ሁሉም ከሰላም በታች ነው ያሉት አቡነ ማትያስ  ምእመናን ሊጠብቁት እንደሚገባ አስረድተዋል ፡፡

"እግዚአብሔር ከምንም በላይ አስቀድማችሁ ሰላምን ፈልጉ ነው ያለውን በመጥቀስም " ሕዝበ ክርስቲያኑ የአምላክ ቃሉን በመጠበቅ ለሀገሪቱ ዕድገትና ልማት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ሊቀጥልበት እንደሚገባ አብራርተዋል ።

በጥምቀት ዋዜማ ከየቤተ መቅደሳቸው የወጡት ታቦታቱ በየአካባቢያቸው ወደ ሚገኙ የባህረ ጥምቀት ስፍራዎች በማምራት በድምቀት የሚከበረው የከተራ በዓል ከቀኑ በሁሉም ዓብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ተከብሮ ውሏል ፡፡