በዓፋር ክልል የሚገኘው ኤርታዓሌ እሳተጎመራ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጎ ሞልቶ እየፈሰሰ መሆኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ ፡፡
ይህንን የኤርታዓሌ ልዩ ክስተት ዛሬ ለዋልታ ያስታወቁት በአራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ኮሌጅ በምድር ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርና በዚሁ ዙሪያ ቅርበት ያላቸው ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ገዛኸኝ ይርጉ ናቸው ፡፡
የዓለምና የአገር ውስጥ ቱሪስቶች መስህብ የሆነው አስደናቂው ኤርታዓሌ እሳተጎመራ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ፍሳሹ ገንፍሎ መልቶና ከዋናው መያዣው ጉድጓድ ወጥቶ በብዛት እየፈሰሰ መሆኑን አመልክተዋል ፡፡
የኤርተዓሌ የቀለጠው ዓለት ፍሳሽ አልፎ ተርፎ የተወሰነ ኪሎ ሜትሮችን ርቆ ሄዶ ሌላ ጕድጓድ ሞልቶ በተጨማሪ ወደ ደቡብ እየፈሰሰ መሆኑን ነው የገለጹት ፡፡
እንደገናም አዲስ ክስተት የተፈጥረው ወደ ኤርታዓሌ መሄጃ በስተቀኝ በኩል አንድ ሌላ ስንጥቅ ተከፍቶ እንደዚሁ ተመሳሳይ ፍሳሽ ወይም ላቫ እየወጣና እየፈሰሰ መሆኑን ጨምረው ፕሮፌሰር ገዛኸኝ አስታውቀዋል ፡፡
ይህንን ክስተት እዛ የነበሩ ሰዎች የክልሉ ባለስልጣናት ነግረውናል ያሉት ፕሮፌሰሩ ፤ከሳተላይትም አንዳንድ መረጃዎችን እያየን ነገሩ እየቀጠለ መሆኑን ነው የተረዳነው ብለዋል ፡፡
አከባቢው ሩቅ ነው በዙም ነዋሪም የለውም ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ በአሁን ሰዓት የሚያመጣው ችግር የለም፤እየቀጠለ ከሄደ ግን አደጋ ሊያመጣ ይችላል ሲሉ ነው ያስጠነቀቁት ፡፡
እንዲያውም ወደ ደቡብ አቅጣጫ ወደ አፍዴራ ከተማ ፍሳሹ እየሄደ በመሆኑ ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለና ካልቆመ አስቸጋሪ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ነው ያመለከቱት ፡፡
ስለሆነም ተሎ ብሎ ወደ ስፍራው መሄድና ለወደፊቱ ለጥናት እንዲያመችም መታየት መመርመር አለበት ነው ያሉት ፡፡
እኛ አገር ሆነ እንጂ ሌላ አገር ቢሆን ወዴያው ሁኔታው እንደ ተሰማ ባንዴ ተሂዶ መረጃው ዓለምን ያዳርስ ነበር ብለዋል ፕሮፌሰሩ ፡፡
ሁኔታው ከመረጃም አልፎ ለዶክሜንተሪ ሊቀርብ የሚችል ክሰተት መሆኑን ነው ያስገነዘቡት ፡፡
የዛሬ 10 ዓመት ተመሳሳይ ክሰተት ተፈጥሮ በሄሊኮፕተር ስንንቀሳቀስ ነበር ያሉት ፕሮሰር ገዛኸኝ አሁን ቦታው ሩቅና በረሃ በመሆኑ ብዙ ዝግጅት ይጠይቃል ሲሉ አስረድተዋል ፡፡
ኤርተዓሌ ረዘም ያለ የእግር መንገድ ያለው ፤በጀትና ሌሎችም ሰፊ ዝግጅት የሚያስፈልገው በመሆኑና ስለከበዳቸው ወደ ስፍራው ለመንቀሳቀስ ብዙም እንዳልቻሉ ነው ፕሮፌሰር ገዛኸኝ ያመለከቱት ፡፡
ስለሆነም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ለወደፊቱ የሚሰጠውን ትምህርት ለመመዝገብና አሁን ሊያስከትል የሚችለው ስጋት ለመከላከል በአፋጣኝ ሊንቅሳቀሱ እንደሚገባቸው ነው ያስገነዘቡት ፡፡
የክልሉ አደጋ መከላከልና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዲ ኑር ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ዔርታዓሌ እሳተ ጎሞራ እየፈሰሰ መሆኑን መስማታቸውንና እስካሁን በሰውና በእንስሳት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አለማድረሱን አረጋግጠዋል ሲል ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ፡፡