ከአፍሪካ ሴት ተማሪዎች ስምንት በመቶ ብቻ የከፍተኛ ትምህርታቸውን እንደሚያጠናቅቁ ተገለጸ

በአፍሪካ ወደ ትምህርት ቤት ከሚላኩ ልጃገረዶች ስምንት በመቶው ብቻ የከፍተኛ ትምህርታቸውን እንደሚያጠናቅቁ ተመለከተ  ።

በጾታ እኩልነትና ትምህርት ላይ ያተኮረ የአፍሪካ ሚኒስትሮችና ባለድርሻ አካላት ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በዚሁ ጉባኤ ከሰሀራ በታች ከሚገኙ አገራት ከ30 በመቶ በላይ ህጻናት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ ለማቃረጥ እንደሚገደዱም ነው የተገለጸው ።

በአብዛኛው የአፍሪካ አገራት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያለው የሴቶች ተሳትፎ ከአንድ ሶስተኛ ያነሰ  መሆኑ ተጠቁሟል ።

እንደ ላይቤርያ ባሉ አገራት ደግሞ የሴት ተማሪዎች መጠነ ማቋረጥ 57 በመቶ መድረሱን ነው የተጠቀሰው፡፡

ስለሆነም የበለጸገች አፍሪካን ለመፍጠር በሴቶች ትምህርት ለውጥ ማምጣት ይገባል ነው የተባለው ፡፡

ስለሆነም በጉባኤው እንደተመለከተው የበለጸገች አፍሪካን በመፍጠር የህዝቦቿን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሴቶች ትምህርት ላይ መስራትይገባል።

የኢፌዲሪ የትምህርት ሚንስትሩ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በትምህርት ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ባደረገችው ጥረት ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

መድረኩ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ልምድ ለማካፈልና በተለያዩ ዘርፎች ሴቶችን ለማብቃት ለምታደርገው ጥረት ግብአት እንደሚሆንም አስረድተዋል።

በጉባኤው ላይ የተገኙት ለጋሽ አገራት፣ ሲቪክ ማሕበራትና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች በህጻናትና ወጣት ሴቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ የተሻለች አፍሪካን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል-(ኢብኮ)።