በኦሮሚያ ክልል 2ሚሊዮን49ሺ የሚሆኑ የድርቅ ተጎጂዎች አስፈላጊው እርዳታ እየተከፋፈለ መሆኑን የክልሉ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ ።
የኦሮሚያ ክልል የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ መኮንን ለሊሳ ለዋልታ እንደገለጹት በክልሉ የአርብቶ አደር ቆላማ አካባቢዎች የሚጠበቀው ዝናብ ባለመዝነቡ ምክንያት በቦረና ፣ በጉጂ፣ ባሌ፣ ምስራቅ ሐረርጌ፣ ምዕራብ ሐረርጌና ምዕራብ አርሲ ዞኖች በአጠቃላይ 2ሚሊዮን 49ሺ የሚደርሱ ሰዎች ለድርቅ ተጋልጠዋል ።
በክልሉ በደጋማና ወይና አደጋ አካባቢዎች የክረምት ዝናብ በመዝነቡ ዓምና በክልሉ ከነበረው 3ነጥብ 7 ሚሊዮን የድርቅ ተረጂዎች ቁጥር እንዲቀንስ ማስቻሉን አቶ መኮንን ጠቁመዋል ።
በክልሉ ለድርቅ በተጋለጡ ዘጠኝ ዞኖች ለተረጂዎች የመጠጥ ውሃ፣ ምግብና የእንስሳት መኖ የማከፋፋል ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን የሚናገሩት አቶ መኮንን ለእርዳታ ሥራ የሚውለውን 186 ሚሊዮን ብር የክልሉ መንግሥት የመደበ መሆኑንና 97 ሚሊዮን ብር የፌደራል መንግሥት ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል ።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ለድርቅ ተረጂዎች እየተከፋፈለ የሚገኘው ከዓምናው ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው የጠቀሱት አቶ መኮንን ለአንድ ተረጂ 15 ኪሎ እህል ፣ 1ነጥብ 5 ጥራጥሬና 45 ግራም ዘይት በመከፋፈል ላይ ይገኛል ።
በአርብቶ አደሩ አከባቢ ድርቁ ያስከተለውን የእንስሳት መኖ እጥረት ለመፍታት የክልሉ መንግሥት በ57 ሚሊዮን ብር ወጪ በሁለት ዙር የእንስሳት መኖን ከማህል አገር በመግዛት የእንስሳት ህይወትን ለመታደግ ጥረት መደረጉን አቶ መኮንን አስገንዝበዋል ።
እንደ አቶ መኮንን ገለጻ በክልሉ በድርቅ የተጋጡ ዞኖች ያጋጠመውን የመጠጥ ውሃ ችግርን ለመቅረፍም 166 የውሃ ቦቴዎች ተሠማርተው በዘጠኝ ዞኖች አገልግሎት እየሠጡ ይገኛሉ ።
በአሮሚያ ክልል እስካሁን ድረስ በክልሉ ለተረጂዎች 2 ሚሊዮን 920ሺ 217 ኩንታል እህል ፣ 272ሺ 823 ጥራጥሬ ኩንታል ፣ 182ሺ 135 አልሚ ምግብ እና 48 ሺ 901 ኩንታል ዘይት መከፋፈሉን አቶ መኮንን ገልጸዋል ።