በደቡብ ክልል መስህብ ቦታዎች የቱሪስት ፍሰትና ገቢ ከሚጠበቀው በላይ መጨመሩን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ ፡፡
የቱሪስት መስህቦች ጥናት፣ ልማትና ግብይት ዋና ስራ ሂደት ባለሙያ አቶ ጌታቸው ጨፈላ እንደገለጹት ፤ በግማሽ በጀት ዓመቱ በታሪካዊ ፣በተፈጥሯዊ ፣በሃይማኖታዊና ባህላዊ መስህቦች 740ሺ 390 ቱሪስቶች ጎብኝተዋል ፡፡
ከነዚሁም 430 ሺህ የአገር ውስጥና 184 ሺህ የውጭ ቱሪስቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ይህም ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የጎብኚዎች ቁጥር በ58 በመቶ መጨመሩን ያሳያል ብለዋል ፡፡
በገቢ ረገድም ከቱሪስቶች 165 ሚሊየን ብር ለማግኘት ታቅዶ 311 ሚሊየን 572 ሺህ 102 ብር መገኘቱን አስታውቀዋል ፡፡
ገቢውም ደግሞ ከታቀደው ከእጥፍ በላይ ገቢ መገኘቱን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል ፡፡
የዚሁ ምክንያትም በተለይም በጥምቀት ፣በመስቀልና በፍቼ ጨምበላላ በዓላት የአገር ውስጥ ቱሪስቶች እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡
የውጭ አገር ቱሪስት ፍሰት ግን በሀገሪቱ ካጋጠመው ሰላም መደፍረስ ጋ ተያይዞ በመጠኑ መቀነሱን በመጠቆም ፡፡
ስለሆነም የውጭ አገር ቱሪስቶች ይበልጥ ለመሳብ በሚድያ ፡በተለያዩ ፖስተሮችና፣ በብሮሸሮችና በህትመቶች ክልሉን የማስተዋወቅ ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ክልሉ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ቱሪስቶች በመሳብ 320 ሚሊየን ብር ለማግኘት መታቀዱን አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል ፡፡