የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የቀብር ስነስርዓት ተፈጸመ

 

የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የቀብር ስነስርዓት ዛሬ በአዲስ አበባ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ።

የካቲት 9 /2009 ዓመተ ምህረት ያረፉት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ዛሬ በተፈጸመው ቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በተወካዮቻቸው ባስተላለፉት የሐዘን መልዕክት ሪቻርድ ፓንክረስት ለኢትዮጵያ ታሪክ፣ ቋንቋና ሙዚየም መበልጸግ ያደረጉት አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን ጠቅሰው ለቤተሰቦቻውና ለወዳጅ ዘመዶቻው መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሊቃነ ጳጳስ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስና ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በቀብር ስነስርዓቱ ላይ በመገኘት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ከሌሎች መስሪያቤቶች የተላከ የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።

ከ1948 ዓመተ ምህረት አንስቶ ለኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን በሥርዓተ ቀብራቸው ላይ የተነበበው የህይወት ታሪካቸው ያመለክታል ።

ምሁሩና ተመራማሪ የነበሩት ሪቻርድ ፓንክረስት 400 ጽሑፎችን ለዓለም አቀፍ መጽሔቶች ያቀረቡ፣ 22 መፅሃፍቶችን በትብብር እና 17 መፅሃፍቶችን በራሳቸው ፣ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ትውፊት የጻፉ ነበሩ ።

የኢትዮጵያ ባለውለታው ሪቻርድ ፓንክረስት የአክሱም ሐውልት ከሮም ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው ይታወቃል  ።

ፕሮፌሰር ፓንክረስት በጣሊያን ወረራ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን የነበሩት የሲልቪያ ፓንክረስት ወንድ ልጅ ሲሆኑ፤ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በ1956 ነበር ፡፡