ለአዲስ አበባ ከተማ መምህራን 5ሺህ ቤቶች ዕጣ ሊወጣላቸው ነው

 

ለመምህራን የተዘጋጁ 5 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በዚህ ሳምንት ዕጣ እንደሚያወጣባቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አበበ ቸርነት እንደገለጹት፤ ቢሮው የተዘጋጁትን ቤቶች የማስተላለፍ ሂደቱን እንዲሁም ቤቶቹ የሚተላለፉበትን የኪራይ ተመን በተመለከተ ነገ ዝርዝር መግለጫ ይሰጣል ።

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን በዚህ ሳምንት በእጣ ለማስተላለፍ ዝግጅት መጠናቀቁንም አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት በበኩላቸው፤17 ሺህ የሚደርሱ መምህራን ዕጣ ውስጥ እንደሚገቡ ገልጸዋል።

 የመምህራኑ ዝርዝር እንደተመዘገቡበት የቤት ዓይነት ወደ ዕጣ ማውጫው ሥርዓት ውስጥ በማስገባት ማውጣት ብቻ ነው የቀረው ብለዋል ።

የተዘጋጁት ቤቶች ስቱዲዮ፣ ባለ አንድ እና ባለ ሁለት መኝታ ቤቶች መሆናቸውን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የቤት ዕድለኞቹ ዕጣ ከወጣላቸው በኋላ በአስቸኳይ ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ለማድረግም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል ።

መምህራኑ በዕጣቸው መሰረት ቤታቸውን ከተረከቡ በኋላ የቤቶች ግንባታ ጽህፈት ቤት እድሳት በማድረግ እንደሚያስረክባቸውም  ማመልከታቸውን  የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዘገባ ያመለክታል ፡፡