በኢትዮጵያ ቀጣናዊ ልማትን በማሳደግ የስደተኞችን ጥበቃ ለማጠናከር የሚረዳ መርሀ ግብር ይፋ ሆነ፡፡
ለመርሀ ግብሩ የአውሮፓ ህብረት፣ የኔዘርላንድስ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበርና የተባበሩት መንግስታት በአጋርነት በመሳተፍ በመደቡት 720 ሚሊዮን ብር የሚከናወን መሆኑ ተመልክቷል፡፡
መርሀ ግብሩ ለስደተኞች ተገቢውን ጥበቃ ለማድረግ የሚያግዙ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ስደተኞችንና በስደተኞችን ጣቢያ አካባቢ የሚገኙ የህረተሰብ ክፍሎችን ተግዳሮቶች ለመፍታት ያግዛል ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ኃላፊ አምደባሳደር ቻንታል ሄቤሬችት እና በኔዘርላንድስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የልማትና ትብብር ምክትል ኃላፊ ሬይና ቡጂስ መርሀ ግብሩ መጀመሩን ትናንት በካፒታል ሆቴል ይፋ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ አገራት የመጡ 800ሺ ያህል ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኑን ህብረቱ አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበል ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ የሚጠበቅባትን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣች መሆኑን ህብረቱ ጨምሮ ገልጿል፡፡ ስደተኞች ወደ ትውልድ አገራቸውና ወደ ሶስተኛ አገር እንዲሄዱ የምታደርገው ጥረትን ህብረቱ አድንቆ ይህንን ለማገዝም ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ከኢትዮጵያ ጎን እየቆመ ነው ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ስደተኞች ከስደተኛ ጣቢያ ውጭ የሚንቀሳቀሱበትን ፖሊሲ መተግበሯ ስደተኞች የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችንና የሥራ ዕድል የሚያገኙበትን አሰራር የሚያግዝ እንደሆነ ተመለክቷል፡፡
መርሀግብሩ ከኤርትራና ከሶማሊያ መጥተው በአፋር፣ በሶማሌና በትግራይ የስደተኞች ጣቢያና በዋና ዋና ከተሞች ለሚገኙ ስደተኞችና በስደተኞቹ ጣቢያ አካባቢ ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚውል ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የዓለም ባንክ 100 ሚሊዮን ዶላር፣የእንግሊዝ የልማት ድርጅት 125 ሚሊዮን ፓውንድ እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች በጀት ፈሰስ በማድረግ በተመሳሳይ መርሀ ግብር እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
(ትርጉም ዳንኤል ንጉሤ)