የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሐኒትና ጤና እንክብካቤ ባለሥልጣን በዘንድሮ የበጀት ዓመት ግማሽ ዓመት ከትንባሆ ጋር በተያያዘ በ57 ተቋማት ላይ ቁጥጥር ማድረጉን አስታወቀ ።
በባለሥልጣኑ የቁጥጥር ፣ መረጃ፣ ዝግጅትናተግባቦት ቡድን መሪ ወይዘሮ አስናቀች አለሙ ለዋልታ እንደገለጹት ባለሥልጣኑ መጋቢት 2007ዓም ያወጣውንና ህዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ትንባሆ ማጨስ የሚከለክለውን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ በ57 ያህል ተቋማት ላይ ቁጥጥር አድርጓል ።
በፌደራል ደረጃ ቁጥጥር የተደረገባቸው ተቋማት ማረሚያ ቤቶች፣ ፋብሪካዎች፣ የመዝናኛ ፣የምግብና የጤና ተቋማት መሆናቸውን የሚገልጹት ወይዘሮ አስናቀች በቁጥጥሩ መሠረት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ የተሠጣቸው ተቋማት እንደሚገኙ ተናግረዋል ።
ባለሥልጣኑ ሁሉም ክልሎች ህዝብ በተሰበሰበበት አካባቢ ትንባሆ ማጨስ የሚከለክለውን መመሪያ በምክር ቤቶቻቸው በማጸደቅ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም እስካሁን ድረስ የአዲስ አበባ አስተዳደር ፣ የትግራይና የአማራ ክልሎች ብቻ በምክር ቤቶቻቸው አፀድቀው የቁጥጥር ሥራ እያካሄዱ መሆኑን ወይዘሮ አስናቀች አስረድተዋል ።
የወጣውን መመሪያ የባለቤትነት ድርሻ በመውሰድ ተግባራዊ በማድረግ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማው ነዋሪዎችና ባለድርሻ አካላት የወጣው መመሪያ ላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሲያከናወን መቆየቱን ወይዘሮ አስናቀች ጠቁመዋል ።
ከክልሎች የትግራይ ክልል መመሪያውን ባለፈው የበጀት ዓመት በምክር ቤቱ በማጸደቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በማካሄድ በአሁኑ ወቅት በተከለከሉ ቦታዎች ላይ ትንባሆ የሚያጨሱ ሰዎችን እስከ መቅጣት ድረስ መድረሱን ወይዘሮ አስናቀች ገልጸዋል ።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባካሄደው ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ በመኖሪያዎች አካባቢ 10 ነጥብ 3 የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ለትንባሆ ጭስ የተጋለጠ ሲሆን 12 ነጥብ 6 በመቶው ህዝብ ደግሞ ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ለሚጨስ ሲጋራ ተጋላጭ መሆኑን ተረጋግጧል ።
እንደ ወይዘሮ አስናቀች ገለጻ ባለሥልጣኑ በተለይም የወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ትንባሆ ማጨስ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን ግንዛቤ እንዲይዝ ለማድረግ በአገሪቱ ከሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ከ 33 ዩኒቨስቲዎች ጋር በመቀናጀት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው ።
በሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 299/2006 መሠረት ህዝብ በሚያዘወትርባቸው አካባቢዎች በሆኑት በጤና ተቋማት፤ በመዋዕለ ህጻናት፣ የትምህርት ተቋማት፣ በምግብ ቤቶች፣ ሆቴሎች፣ መጠጥ ቤቶች፣ የምሽት ክለብ፣ ካፌዎች፣ መዝናኛ ክበብ፣ ማረሚያ ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢያ እና የመንግስት እና የግል መስሪያ ቤቶች ትንባሆን ማጨስ እንደሚከለክል ተደንግጓል ።
ኢትዮጵያ የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣውን የትንባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽን ጥር 21 ፤2006 ዓም ተግባራዊ ለማድረግ የስምምነት ፊርማዋን በማኖር ዜጎችን ትንባሆ ከሚያመጣው የጤና ጠንቆች ለመከላከል እየሠራች መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።