የ10ኛና 12ኛ ክፍል ተፈታኞች ምዝገባ በኢንተርኔት እንደሚደረግ ኤጀንሲው አስታወቀ

 

የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ተፈታኞች ምዝገባ በቀጣዩ ዓመት በኢንተርኔት ኦንላይን ሊደረግ ነው የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ምዘና ኤጀንሲ ገለጸ ።

በኤጀንሲው የፈተናና ምዘና ውጤት ጥንቅር ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ አበራ፤የኢንተርኔት ምዝገባው በቀጣዩ ዓመት ተግባራዊ ለማድረግ ሙኮራ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ የኢንተርኔት ምዝገባ አሁን ላይ በአዲስ አበባ በ152 የግልና የመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ የሙከራ ስራ የጀመረ ሲሆን፤ ከነዚሁም በ146 ትምህርት ቤቶች ላይ ጥሩ ውጤት ታይቷል ብሏል።

እንደ አቶ ዮሴፍ ገለጻ የኦንላይን ምዝገባው ከምዝገባ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ስህቶቶችንም ለመቀነስ ያግዛል ።

ኢትዮጵያ ለ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሄራዊ ተፈታኞች የምዝገባ ወረቀት (ፎርም) ከለንደን የምታስገባ ሲሆን፤ ለአንድ ፎርም አንድ ፓውንድ የሚጠጋ ሂሳብ ታወጣለች ነው ያሉት ።

የኦንላይን ምዝገባው መጀመር ለወረቀት ፎርም ግዥ የሚወጣውን በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ማዳን እንደሚያስችል ገልጸዋል ።

ሁሉም የሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች የኦንላይን ምዝገባውን ለማከናወን የሚያስችል የኢንተርኔት አገልግሎት እንዳላቸውም ዳይሬክተሩ አመልክተዋል-(ኤፍ ቢ ሲ) ።