በቆሼ በደረሰው የቆሻሻ መደርመስ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው 16 የግል ባለ ይዞታዎች የይዞታ ካርታ ርክክብ ተደረገ።
ባለ ይዞታዎቹ ከካርታው ባሻገር ለወደመባቸው ንብረት የካሳ ክፍያ እና የአንድ አመት የቤት ኪራይ ክፍያም ዛሬ ተፈፅሞላቸዋል።
በኮልፌ ቀራንዮ ወረዳ 2 ጀሞ ቁጥር 2 የጋራ መኖሪያ ቤት ማስፋፊያ የለማ ቦታ ላይ ነው ለ16 የግል ባለ ይዞታዎቹ መሬት የተሰጣቸው።
ለ14ቱ ባለይዞታዎች 175 ካሬ ሜትር መሬት የተሰጣቸው ሲሆን፤ ሁለቱ ለእያንዳንዳቸው 250 እና 200 ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቷቸዋል።
የህጋዊ ይዞታ ባለቤት የነበሩና በአደጋው ህይወታቸው ላለፈ ዜጎች 13 ልጆችም ባለ ሁለት ፎቅ ህንፃ ለመገንባት በዛሬው እለት የመሰረት ድንጋይ በጀሞ ቁጥር 2 የጋራ መኖሪያ ቤት ማስፋፊያ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
54 ለሚሆኑ ተከራዮችም የ10/90 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የቁልፍ ማስረከብ ስነ ስርአት ተካሂዷል ።
ድጋፍ የተደረገላቸው ተጎጂ ቤተሰቦች የለማ ቦታ መሰጠታቸው እና የቤት ግምት ካሳ እና የአንድ አመት የቤት ኪራይ ክፍያ መፈፀሙ እንዳስደሰታቸው ገልፀው፥ መንግስት በተሰጣቸው ቦታ ላይ የሚገነባላቸው ቤት በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ጠይቀዋል።
የካርታ ርክክቡን ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ በበኩላቸው፤ በዘላቂነት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ባለ ይዞታዎችም የተሰጣቸውን ቦታ ለሌላ ሰው አሳልፈው ባለመስጠት ከአካባቢው ህዝብ እና መንግስት ጋር በትብብር እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መጋቢት 23 2009 በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው (በህገወጥ መንገድ የሸራ እና የጭቃ ቤት ሰርተው ይኖሩ ለነበሩ ነዋሪዎች) በንፋስ ስልክ ላፍቶና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች ውሰጥ በ24 ሚሊየን ብር ወጪ የተሰሩ 110 የመኖሪያ ቤቶችን ለተጎጂዎች ማስረከቡ ይታወሳል-(ኤፍ ቢ ሲ) ።