ባለሥልጣኑ 2ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ የሦስት መንገዶች የኮንትራት ስምምነት ፈጸመ

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በአጠቃላይ  በ2ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ  የሚከናወኑ የሦስት መንገዶች ግንባታ ለማከናወን  ከአገር  ውስጥ  የመንገድ  ተቋራጮች ጋር  የኮንትራት ስምምነት ማድረጉን አስታወቀ ።  

ባለሥልጣኑ በደቡብ ክልል የትሩሚ -ኦሞ የ63 ኪሎሜትር መንገድ ፕሮጀክትና በኦሮሚያ  ክልል የሮቤ-ጋሪሳ የ60 ኪሎሜትር  የመንገድ ፕሮጀክትን የግንባታ ሥራ በጋራ  ከሚያካሄዱት   የአፍሮ ጺዮንና የራማ  ኮንስትራክሽን ኩባንያዎች  ጋር ስምምነት ፈጽሟል ።

በተጨማሪም ባለሥልጣኑ የጋምቤላ-አሊያ የ78  ኪሎሜትር የመንገድ ፕሮጀክትን ለማከናወን ከኦርኪ ላንድ የቢዝነስ ግሩፕ ጋር  የኮንትራት ፊርማውን  አኑሯል ።     

ባለሥልጣኑ ስምምነት ካደረገባቸው ሦስት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል  የጋምቤላ – አሊያ የመንገድ ፕሮጀክት  በ1 ቢሊዮን ብር ወጪ  የሚከናወን መሆኑ የተመለከተ ሲሆን የትሩሚ -ኦሞ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት 897 ሚሊዮን ብር የሮቤ -ጋሪሳ የመንገድ ፕሮጀክት  770  ሚሊዮን  ብር ወጪ ለማካሄድ ከስምምነት ላይ ተደርሷል ።

የባለሥልጣኑ  የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ በበኩላቸው  ሦስቱም  የመንገድ ፕሮጀክቶች  የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አካል  መሆናቸው የአካባቢው ነዋሪዎችን ምርቶቻቸውን ለገበያ በማውጣት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ናቸው ።

ከባለሥልጣኑ ጋር ስምምነት የፈጸሙት የአገር ውስጥ ኩባንያዎች በመንገድ ግንባታ ሥራ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ሲሆን የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ  ለማጠናቀቅ  ተስማምተዋል ።   

በኮንትራት  ስምምነቱ መሠረት  የመንገድ ፕሮጀክቶቹ  ድህረ ጥገና ሥራ  በስምምነት ውሉ መካተቱን  ዋልታ ሚዲያ ኮርፖሬት ዘግቧል ።  

(ትርጉም በሰለሞን ተስፋዬ)