የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ ካቶሊካዊት ቤትክርስቲያን፣ የወንጌላዊት መካነየሱስ፣ የቃለሕይወትና የኃይማኖቶች ሕብረት አባቶች የፋሲካ በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ ገለጹ፡፡
ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ከትራፊክ አደጋ ነፃ የሆነ የትራፊክ ምልልስን ዕውን ለማድረግ እንዲቻል ሕብረሰተሰቡ፣ የትራፊክ ባለሙያዎች አሽከርካሪዎች ጥንቃቄ በማድረግ አደጋውን ለመቀነስ እንዲቻል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሀገሪቱ የተከሰተውን ድርቅ ለመካላከል እንዲቻል ቤተክርስቲያኗ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልና ሕብረተሰቡም ለወገኑ እንዲደርስ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ርዕሰሊቃነጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለኃይማኖት አባ ማትያስ ቀዳማዊ እንደገለጹት በማሕበረሰቡ ሥር ሰደው ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ሐይማኖትና ልማትን አጣምሮ መያዝና መፅናት አማራጭ የሌላቸው መፍትሄዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ብፁዕነታቸው አክለውም መላው የሀገሪቱ ሕዝቦች በኑሯቸውና በሕይወታቸው መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚችሉት እንደቀድሞ አባቶቻቸው በራስ በመተማመን፣ በልበ ሙሉነት፣ በትጋት፣ ቅንነት፣ ፍቅር፣ ስምምነት፣ በእኩልነትና፣ በወዳጅነት፣ በሰላምና በአንድነት፣ በመቻቻልና በአብሮነት፣ ሆነው በሚያስመዘግቡት የልማት ውጤት እንደሆነ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቃለሕይወት ቤተክርስቲያን ፕሬዝዳንት ዶክተር እያሱ ኤልያስ በበኩላቸው በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ችግር
የተጎዱትን ወገኖችን ለመርዳት ከመንግስት ጋር በመተባበር የሚደረገውን ጥረት ሁሉም ዜጋ በሚችለው መልኩ እንዲያግዝ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የትራፊክ አደጋ የዜጎችን ሕይወት በመቅጠፍና የሀገሪቷን ገጽታ በማበላሸት እየተባባሰ በመምጣጡ ችግሩን ለመቅረፍ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን መካነየሱስ ቤተክርቲያን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በወንጌልና በስነምግባር ትምህርት እንዲሁም በስልጠና ከባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ቄስ ዮናስ ይገዙ ገልጸዋል፡፡
የታረዙትን ማልበስ የተራቡትን ማብላት፣ ጉዳት የደረሰባቸውን መንከባከብና በተለይም በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ እንዲቻል ጥረት ማድረግ ይገባል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያውያን ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ፃድቁ አብዶ ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ በተከሰተው ድርቅ የተጋለጡ ዜጎችን በማሰብ ከእግዚአብሔር ስጦታ በማካፈል እጆችን በመዘርጋት ዜጎች ከዚህ ችግር እንዲላቀቁ ህብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ፓስተር ፃድቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡