ባለሥልጣኑ በምህንድስና  ለተመረቁ 900   ወጣቶች የሥራ ዕድል  ለመፍጠር  እየሠራ ነው

በአዲስ  አበባ ከተማ  ለሚገኙ በምህንድስና  ለተመረቁ  900  ወጣቶችን  በተለያዩ  የሥራ ዘርፎች ለማሠማራት እየሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን አስታወቀ ።
በባለሥልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስጢፋኖስ ብስራት ለዋሚኮ እንደገለጹት ባለሥልጠኑ በዘንድሮ የበጀት ዓመት በሲቪልና በውሃ ቴክኖሎጂ ተመረቀው ሥራ ያጡ  900 ወጣቶችን  በማደራጀት  በፍሳሽና በውሃ መሥመር ዝርጋታ ሥራዎች ለማሠማራት እየተንቀሳቀሰ ነው ።
ባለሥልጣኑ በመጀመሪያ ዙር 452 የሚሆኑ ወጣቶችን በ51 ማህበራት እንዲደራጁ በማድረግ   የአሥር ቀን ሥልጠና መሥጠቱን የጠቆሙት አቶ አስጢፋኖስ ወጣቶቹ ብድር ተመቻችቶላቸው ወደ ፕሮጀክት ሥራቸው  በመግባት ላይ ናቸው ብለዋል ።
ወጣቶቹ ወደ ተግባር ሥራ ሲገቡ የመጀመሪያ ጊዜያቸው በመሆኑ ባለሥልጣኑ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ፣ የማማከር እገዛን እንደሚያደርግላቸው የገለጹት አቶ አስጢፋኖስ  በየጊዜውም  የሥራ አፈጻጻማቸው ላይ ቁጥጥር እንደሚያደርግ አስረድተዋል ።
ባለሥልጣኑ በምህንድስና ዘርፍ ለተመረቁና ሥራ ያጡ ወጣቶችን በተለያዩ ፕሮጀክቶቹ  ተደራጅተው እንዲሠሩ የማድረግ እንቅስቃሴውን አጠናክሮም እንደሚቀጥል አቶ አስጢፋኖስ አያይዘው ገልጸዋል ።
የአዲስ አበባ ጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ኢንተርፕራይዝ ቢሮ በምህንድስና የተመረቁ ሥራ አጥ ወጣቶችን  በመመልመል ፣ አስፈላጊውን  ግብዓት በሟሟላት ተደራጅተው እንዲሠሩ የማድረግ ሚናውን ተጫውቷል ።