ለትንሳኤ በዓል ህገወጥ እርድ እንዳይፈጸም የነዋሪዎች ትብብር ተጠየቀ 

የትንሳኤ በዓልን ተከትሎ ሊፈጸም የሚችለውን ህገወጥ እርድ ለመከላከል ነዋሪዎች ትብብር እንዲያደርጉ ተጠየቀ።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ በእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ግብይት ላይ የዋጋ ጭማሬ መኖሩን በምስራቅ ጎጃም ዞን አንዳንድ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የመቀሌ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፀጋይ ገብረኪዳን በሰጡት ጋዜጣዊ መግላጫ ላይ እንዳሉት፣ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ህገወጥ እርድን የሚያከናውኑ ግለሰቦችን ለመቆጣጠር የከተማው ነዋሪዎች የራሳቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል።

ህገወጥ እርድን በመከላከል ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን መቀነስ እንደሚቻል የገለጹት ኃላፊው፣ ሕብረተሰቡ የራሱን አስተዋጽኦ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላትጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።

በከተማው አንዳንድ የስጋ ነጋዴዎች የሚፈጽሙት ህገወጥ እርድ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ የሕብረተሰቡ ጤና እንዳይጎዳ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ የመከላከሉ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን የነዋሪዎች አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማው የሚገኙ ሆቴሎችና ምግብቤቶችም በህገ ወጥ ዕርድ የሚታረዱ እንስሳትን እንዳይጠቀሙ አሳስበዋል።

በጤና ቁጥጥር፣ በጽዳትና ውበት እንዲሁም በፀጥታ ሥራ የተሰማሩ ሠራተኞች በሰጡት አስተያየት እንዳሉት፣ ህገወጥ እርድን ለመከላከል ተዘጋጅተዋል።

በከተማው የጽዳትና ውበት ሠራተኛ ወጣት ገብረዮሐንስ ኃይለኪሮስ እንዳለው፣ ህገወጥ እርድ የሰዎችን ጤና ከመበከሉ በተጨማሪ በከተማው ጽዳትና ውበት ላይ የራሱን ችግር እየፈጠረ ይገኛል።

ለዚህም የትንሳኤ በዓልን ተከትሎ የከተማው ጽዳትና ውበት በህገወጥ የእንስሳት ተረፈ ምርት እንዳይበላሽ ድርጊቱ ሲፈጸም ለፀጥታ አካላት ከመጠቆም ባለፈ ጽዳትን ለማስጠበቅ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በከተማው ውስጥ ጨለማን ተገን በማድረግ  ህገወጥ እርድ የሚያከናውኑ በሥጋ ንግድ የተሰማሩ አንዳንድ ነጋዴዎች እንዳሉ የተናገሩት ደግሞ በከተማው የጤና ተቆጣጣሪ ሠራተኛ አቶ መሀሪ ነጋሽ ናቸው።

የከተማው የጤና ተቆጣጣሪ አካላት በበዓሉ ምክንያት በሚከናወኑ ህግ ወጥ እርድ የሕብረተሰቡ ጤና እንዳይጎዳ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ግብይት ላይ የዋጋ ጭማሬ መኖሩን በምስራቅ ጎጃም ዞን አንዳንድ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በዞኑ የጎዛምን ወረዳ የእነራታ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ብናልፍ ሰውነት እንዳሉት፣ በግ ለመግዛት ደብረማርቆስ ከተማ ወደሚገኘው የበግ ገበያ ከሁለት ቀን በላይ ቢመላለሱም በያዙት ገንዘብ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

"ባለፈው ዓመት በገናና ፋሲካ በዓል ላይ የነበረው ጭማሪ ትልልቅ በጎች ላይ ነበር" ያሉት አቶ ብናልፍ፣ በዚህ ዓመት በሁሉም የበግ አይነቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ተናግረዋል።

እርሳቸው እንዳሉት በአካባቢው ትልቅ በግ ከ3 ሺህ ብር በላይ፣ መካከለኛ በግ ከ2 ሺህ ብር በላይ እየተሸጠ ነው።

በዚሁ ወረዳ የጥጃን ቀበሌ ነዋሪ አቶ አለሁበል አድማስ እንዳሉት ባለፈው ዓመት ዘጠኝ ሺህ ብር የገዙት መካከለኛ በሬ ሰሞኑን 11ሺህ ብር እየተሸጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በየዓመቱ በጎችን እያደለቡ እንደሚሸጡ የተናገሩት የማቻከል ወረዳ የገነቴ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገናናው ታደለ በበኩላቸው፣ በዚህ ዓመት በደንብ ከደለቡ በጎች እስከ 1 ሺ 5 መቶ ብር የሚደርስ ጭማሬ መታየቱን ገልጸዋል።

የእንስሳት መኖ እጠረትና ዋጋ መጨመር ለዋጋ ልዩነት መፈጠር አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል።

የዞኑ ንግድና ኢንዱስትሪ ገበያ ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰለሞን አሞኘ በበኩላቸው "ለፋሲካ በዓል በእንስሳትም ሆነ በእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል" ብለዋል።

አሁን ባለው ገበያ ትልቅ በግ በአማካኝ ከ2 ሺህ 500 ብር በላይ፣ መካከለኛ በግ ከ2 ሺህ ብር በላይና ዝቅተኛ በግ ደግሞ አንድ ሺህ 5 መቶ ብር እየተሸጠ ነው።

ትልቅ የደለበ በሬ 14 ሺህ ብር፣ መካከለኛ ከ11ሺህ ብር በላይ ዝቅተኛ ከ7ሺህ ብር በላይ እየተሸጠ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ ትልቅ ደሮ 150 ብር፣ አንድ ኪሎ ግራም ቅቤ 200 ብር፣ እንቁላል ሦስት ብር በአማካኝ እየተሸጠ ይገኛል።

ዋጋው አምና በፋሲካ በዓል ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በበሬ እስከ ሦስት ሺህ፣ ከበግ እስከ አንድ ሺህ እንዲሁም ከዶሮ ከ30ብር በላይ ጭማሪ መታየቱን አስረድተዋል።

በአንጻሩ በበዓል ገበያ በቀይ ሽንኩርት ላይ እስከ አራት ብር፣ በነጭ ሽንኩርት እስከ አምስት ብር ድረስ ቅናሽ መኖሩን ነው የገለጹት።

በተወሰነ ደረጃ የአቅርቦት እጥረት መኖሩ ለዋጋው ጭማሪ ምክንያት መሆኑን አቶ ሰለሞን አመልክተዋል- (ኢዜአ ) ፡፡