የንግድ ቤቶች በውጭ ሃገራት ቋንቋ መሰየማቸው የሀገሪቱን ባህልና ቋንቋ ያኮስሳል ሲሉ በኮተቤ ዩኒቨርስቲ የስነ ፅሑፍ መምህር አስገነዘቡ ፡፡
በኮተቤ ዩኒቨርስቲ የስነ ፅሑፍ መምህር አቶ የሻው ተሰማ ለዋልታ እንደገለጹት ፤አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች የንግድ ስያሜአቸውን በውጭ ቋንቋ ያደረጉ በርካታ የንግድ ቤቶችና ሌሎች ተቋሞች ይገኛሉ ፡፡
እነዚህ የንግድና ልዩ ልዩ ተቋሞች በውጭ ሃገራት ቋንቋ መሰየማቸው የሀገሪቱን ባህልና ቋንቋ የሚያኮስስ መሆኑን ነው ያስረዱት ፡፡
በተለያዩ የሚዲናዋ አካባቢዎች ተዟዙሮ ዋልታ ያነጋገራቸው ኗሪዎችም በስያሜዎቹ ደስተኞች እንዳልሆኑና ግራ እንደሚጋቡ ነው ያመለከቱት፡፡
ችግሩን ለመቅረፍም በተለይም የመንግስት አካላትን ጨምሮ ሁሉም ህብረተሰብ ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት ብለዋል፡፡
በሌላም በኩል ቻይና መንደሮቿን በውጭ ሀገራት ቋንቋ እንዳይሰየሙ የሚከለክል ህግ በፈረንጆቹ በ2016 አውጥታለች፡፡
ኩባንያዎቿ በተለያዩ የዓለም ሃገራት ሲሰሩም ቻይንኛን የመጠቀም ባህል አላቸው ፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙ የቻይና ኩባንያዎችም ይህንን ያደርጋሉ፡፡
ይህ ልማድ በሩቅ ምስራቅ ሃገራት ዘንድም በስፋት ይስተዋላል፡፡
በአንፃሩ ኢትዮጵያ ደግሞ በተለይም የባህር ማዶ ቋንቋ የሚጠቀሙ የንግድ ቤቶች ስያሜን በተመለከተ ምንም ዓይነት ክልከላ አለማድረጓ ሊታረም የሚገባው አገራዊ ጉዳይ ይሆናል ፡፡