ኢትዮ አሜሪካ ተርሸሪ ሆስፒታል 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወጪ ለመገንባት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የመሰረተ ድንጋይ አስቀመጡ ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በአሜሪካና በተለያዩ የአለም ሃገራት በሚገኙ የህክምና ዶክተሮች በአዲስ አበባ ለሚገነባው ተርሸሪ ሆስፒታል የመሰረት ድንጋይ ዛሬ አስቀምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሰረት ድንጋዩን ባስቀመጡበት ወቅት እንዳሉት፤ በተለያዩ የአለም ሃገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው ገብተው በሙያቸው እንዲሰሩ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል።
አሁን ላይ ከኢኮኖሚ እድገቱ እና ከአኗኗር ዘይቤ ጋር ተያይዞ እየተከሰቱ ያሉ በሽታዎች ውስብስብ ከመሆናቸው አንጻር የሆስፒታሉ ግንባታ አስተዋጽኦው ከፍ ያለ ይሆናል ብለዋል።
አዲስ አበባ የበርካታ አለም አቀፍ ተቋማት እንደመሆኗ መጠን ደረጃውን የጠበቀ የህክምና አግልግሎት የሚሰጥ የህክምና ተቋም እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል።
ይህ በሶስት አመታት ውስጥ ይጠናቀቃልም የተባለው ዘመናዊ ሆስፒታል ደረጃውን የጠበቀ የህክምና ከመስጠት ባለፈም ለህክምና የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ያስቀራል ተብሎም ይጠበቃል።
በኢትዮጵያና በጎረቤት ሃገራት ልዩነት የሚፈጥር የህክምና ማዕከል እንደሚሆን የሚጠበቀው ሆስፒታሉ ተመርቀው ወደ ስራ ለሚገቡ የህክምና ባለሙያዎች ትልቅ እገዛ ያደርጋልም ተብሏል።
ሆስፒታሉ ለህሙማን ማስታመሚያ 300 አልጋዎች ሲኖሩት ስምንት የቀዶ ጥገና ክፍሎችንም ይይዛል።
ካንሰርን ጨምሮ ለሌሎች በሽታዎችም የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ተገልጿል ፡፡
ከአምስት አመታት በፊት በ12 የህክምና ዶክተሮች የተጀመረው የኢትዮ አሜሪካ ተርሸሪ ሆስፒታል ግንባታ ጥንስስ ሃሳብ አሁን ላይ 260 አባላትን ይዟል።
አባላቱ ከኢትዮጵያ፣ ከመካለኛው ምስራቅ፣ ከአሜሪካ እና ከሌሎች ሃገራት የተውጣጡ የህክምና ባለሙያዎች ናቸው-(ኤፍ ቢ ሲ) ።