የጀርሞችን መድሐኒት የመላመድ ችግር መቀነስ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል – ኤምኤስኤች

የጀርሞችን የፀረተሕዋስያን መድሐኒት የመላመድን ችግር መቀነስ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ኤምኤስኤች (The Management Sciences for Health-MSH) ገለጸ፡፡

ድርጅቱ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ሲምፖሲየም እንደተመለከተው የፀረተሕዋስያን መድሐኒቶችን ከልክ በላይ መጠቀምና ዝቅተኛ በሽታን የመከላከል ትግባር ዝቅተኛ መሆን ጀርሞች የፀረተሕዋስያን መድሐኒቶችን የመላመድ ዕድልን እንደሚያባበብሰው ተጠቁሟል፡፡

የፀረተሕዋስያን መድሐኒቶችን የተላመደ በሽታን መከላከል ከፍተኛ ወጪ ያስወጣል፤ መድሐኒቶቹ በቀላሉ አይገኙም፤ ሕክምናው ረጅም ጊዜ ይፈጃል፤ ውጤማነቱም አነስተኛ ነው፤ ከዚህም በላይ በሕይወት የመኖር ዕድሉም አነስተኛ እንደሆነ በሲምፖዚየሙ ላይ ተመልክቷል፡፡

በኤምኤስኤች የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ንጉሱ መኮንን በሲምፖዚየሙ የመዝጊያ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ጀርሞች መድሐኒቶችን የመላመድ ችግር ለመቀነስ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች ቢሆኑም ለጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት በመስጠት ረገድ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደረጉ ይገባል ብለዋል፡፡

ሲምፖዚየሙ ጀርሞች መድሐኒቶችን የመላመድ ችግር ለመቀነስ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ይበልጥ ማጠናከርን ዓላማነት ያነገበ እነደሆነም ዶክተር ንጉሱ አክለው ገልፀዋል፡፡

በዕለቱ ጥናት አቅራቢዎችና አወያዮቹ ከተሳታፊዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ታዋቂ ምሁራን፣ የጤና ባለሙያዎች፣ አጥኝዎች፣ የሕብረተሰብ ጤና ሳይንስ ከፍተኛ ባለሙያዎች ሲምፖዚየሙን ታድመዋል፡፡

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ በ2006 ዓ.ም. በተደረገው ጥናት ከ480 ሺህ የሳንባ ሕሙማን 3 ነጥብ 3 በመቶ ያህሉ  የፀረተሕዋስያን መድሐኒቶችን የተላመዱ ጀርሞች እንዳሉባቸው ታውቋል፡፡ በተመሳይ ሁኔታም በ105 አገሮች በተወሰደ ናሙና ከ9 ነጥብ 7 በመቶ ያህል ሕዝቦች የሳንባ በሽታን የፀረተሕዋስያን መድሐኒቶችን እንደተላመዱ ተገልጻል፡፡

ኤምኤስኤች የጤና አገልግሎቶችን ለማሻሻል፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ለማድረግ በ1963 ዓ.ም. እንደተመሰረተና እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ150 አገሮች አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡

ሲምፖዚየሙ “የጀርሞች ፀረ ተሕዋስያን መድሐኒቶችን የመላመድ  ዕድገት፣ ተግዳሮትና የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎች” በሚል መሪ ቃል መከበሩን ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽንስ ኮርፖሬት ዘግቧል፡፡