በደቡብ ክልል 2,265 ጎዳና ተዳዳሪዎች በተለያዩ ሙያዎች ሠልጥነው ተመረቁ

የደቡብ ክልል መንግሥት ከኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ደቨሎፕመንት አሶሲየሽን ማሠልጠኛና መልሶ ማቋቋሚያ ማዕከል ጋር በመተባበር በተለያዩ ከተሞች በልመናና በጎዳና ተዳዳሪነት ህይወት የሚኖሩትን 2,265 ወጣቶች በተለያዩ ሙያዎች አሠልጥኖ አስመረቀ፡፡

በምረቃው ሥነ ሥርዓት የፌዴራል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አብዱልፈታ አብዱላሂ፣የፈዴራል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትር ወ/ሮ ደሚቱ ሀምቢሣ፣ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር አቶ ምትኩ ካሳ እና ሚኒስቴር ዴኤታዎች፣ ከክልልና ከፌዴራል መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝዋል፡፡

ሠልጣኞቹ በ10 የሙያ መስኮች ለ6 ወራት ሥልጠና ተከታትለው በየሙያቸው ተደራጅተው መሥራት የሚያስችል ክህሎት ማግኘታቸውም ገልጿል፡፡

ሠልጣኞቹ ያሳለፉበት የጎዳና ህይወት አስከፊ ቢሆንም አሁን የሰለጠኑበትን ክህሎት በመጠቀም በልማት ሥራ ተሠማርተው ህይወታቸውን በመለወጥ ለራሳቸውና ለሀገራቸውም ጠቃሚ ዜጎች መሆን የሚችሉበት የአዲስ ምዕራፍ ጅማሬ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

 ተመራቂዎቹ በዶሮ እርባታ፣በእርሻና ከብት ማደለብ፣በእንጨትና በብረታ ብረት፣በግንባታ ሥራ፣ በመብራት መስመር ዝርጋታ፣በአውቶመካኒክና በአውቶ ሰርቪስ፣በምግብና በውበት ሥራ፣በጨርቃጨርቅና አልባሳት ሙያዎች በመሰልጠናቸው ወደየአካባቢያቸው እንደተመለሱ ሥራ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡

እነዚሁ ወጣቶች በቀጣይነት ውጤታማ እንዲሆኑ 19 መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት በጋራ እየሠሩ በመሆናቸው ሁሉንም ተመራቂዎች ወደየመጡበት አካባቢ በመመለስ አደራጅቶ ወደ ሥራ ለማሰማራት ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡

በማሰልጠኛው ግቢ በየጊዘው የሚመጡ ሠልጣኞች ህክምና የሚያገኙበትን ዘመናዊ ክሊኒክ ተመርቆ ሥራ እንዲጀምር መደረጉንም ከክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተገኘዉ መረጃ ያመለክታል፡፡