ኢትዮጵያ የጋምቤላው ማጃንግ ዞን ጥብቅ ደን በዩኔስኮ አስመዘገበች

ኢትዮጵያ በጋምቤላ ብሔራዊ ክልል የሚገኘውን የማጃንግ ጥብቅ ደን ባዮስፌር አካባቢ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አስመዘገበች።

የማጃንግ ጥብቅ ደን ባዮስፌር አካባቢ በዩኔስኮ መመዝገቡን ይፋ ያደረጉት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያና የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋት ሎዋክ ቱት ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ በጋራ በሰጡት መግለጫ ነው።

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን እንዳገለጸት፤ ኢትዮጵያ እስካሁን አራት የባዮስፌር ጥብቅ አካባቢዎችን አስመዝግባለች የዛሬው ደግሞ  አምስተኛ ነው።

መቀመጫውን ፈረንሳይ ፓሪስ ያደረገው የዩኔስኮ የሰውና ባዮስፌር ፕሮግራም ዓለም አቀፍ አስተባባሪ ካውንስል ከሰኔ 5 እስከ 8 ባካሄደው 29 ጉባኤ ላይ የማጃግ ደን ባዮስፌር መስፈርቱን ያሟላ በመሆኑ በድርጅቱ እንዲመዘገብ ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውቀዋል።

የዩኔስኮ ባዮስፌር አስተባባሪ ኮሚቴ ያስቀመጠውን መስፈርት በማሟላቱ በዚህ ዓመት ለምዝገባ የበቃው የማጃንግ ባዬስፌር ጥብቅ አካባቢ የቆዳ ስፋቱ 225 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ  ነው።

ስፍራው ከ550 በላይ የዕጽዋትና ተክሎች፣ 33 አጥቢ እንስሳት፣ 130 አዕዋፍ እና 20 ተሳቢ እንስሳት የሚገኙበት መሆኑነ ነው የተመለከተው ።

ከነዚህ ውስጥ 39 የሚሆኑ ዝርያዎች ለመጥፋት በከፍተኛ አደጋ ውስጥ ያሉ በመባል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመዝግበው የሚገኙበት ነው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋት ሎዋክ ቱት በበኩላቸው የማጃንግ ደን ባዮስፌር ባለ ጣዕም የጫካ ቡና፣ የዱርና የጫካ ማር፣ ኮረሪማ፣ ቀይና ጥቁር በርበሬ፣ እንሰትና ሌሎች የግብርና ውጤቶች የሚመርትበት አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል ።

ድንቅ የሆነው መልካ ምድሩ፣ ጥቅጥቅ ደኑ፣ ሀይቁ፣ የአካባቢ ማህበረሰብ ያልተበረዘ ጥንታዊ ባህሉ ስፍራውን ለቱሪዝም የተመቸና ተመራጭ እንደሚያደርገውም አስረድተዋል።

በማጃንግ አጎራባች የሚገኘውን ጥብቅ ደን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ የተፈጥሮ ሐብት ስፍራዎች የአካባቢ ክብካቤና ጥበቃ ስራን በማጠናከር ወደፊት የማስመዝገብ ስራ እንደሚቀጥል ርእሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

በማጃንግ አካባቢ ላለፉት አራት ዓመታት ለምዝገባው ተፈላጊ መስፈርትን ማሟላቱን የሚያረጋግጥ ጥናት ሲካሄድ እንደነበርም አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ በደቡብ ክልል የሚገኘውን የካፋ ዞን ባዮስፌር ሪዘርብንና በኦሮሚያ የሚገኘውን የያዩ የቡና ጫካን በ2002 ዓም ማስመዝገቧን አስታውሰው በደቡብ የሸካ ባዮስፌር ደግሞ በ2004 ዓ.ም በዩኔስኮ መመዝገቡን ተጠቅሰዋል ።

በተጨማሪም በአማራ ክልል የሚገኘው የጣና ሀይቅ የባዮስፌር ጥብቅ ስፍራም በ2007 ዓ.ም በዩኔስኮ ማስመዝገብ መቻሏን ነው የተመለከተው ።

በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም በ120 አካባቢዎች 669 ስፍራዎች የባዮስፌር ጥብቅ አካባቢዎች የኔትዎርክ አካል ሆነው ተመዝግበዋል-(ኢዜአ) ።