የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተረከባቸው የ40/60 ቤቶች የፊታችን ቅዳሜ እጣ ይወጣባቸዋል

የኢትዮጵያ ባንክ የተረከባቸው የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሀምሌ 1 2009 ዓ.ም እጣ ይወጣባቸዋል።

የእጣ ማውጣት ስነ ስርዓቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል አዳራሽ እንደሚከናወን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለፋና ብሮድካስቲንግ በላከው መግለጫ አመላክቷል።

በአጠቃላይ የእጣ አወጣጥ ስነስርአቱ ዙሪያም ሰኔ 29 ቀን 2009 ዓ.ም ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ በ40/60 የቤት ልማት መርሃ ግብር በሶስት ምዕራፍ የ39 ሺህ 229 ቤቶች ግንባታን በ13 ሳይቶች እያከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል።

ኢንተርፕራይዙ በግንባታ ላይ ካሉ 13 ሳይቶች መካከል በሰንጋተራ እና ክራውን ሳይቶች ግንባታቸው የተጠናቀቁ 1 ሺህ 292 ቤቶችን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በተገኙበት መጋቢት 2 2009 ዓ.ም ማስመረቁ ይታወሳል።

በሁለቱ ሳይቶች የሚገኙ 876 ቤቶችንም በቅርቡ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማስረከቡ አይዘነጋም።

ርክክብ ያልተደረገባቸውን ሁለት ብሎኮች ለመረካከብና በቅርቡ ስራውን ለመጨረስም ከባንኩ ጋር እየተሰራ መሆኑን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሁለቱ የግንባታ ሳይቶች ከተገነበቱት 1 ሺህ 292 ቤቶች 972ቱ መኖሪያ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ ናቸው።

ግንባታቸው ተጠናቆ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ርክክብ የተፈፀመባቸው ቤቶች የውሃ፣ የመብራት፣ የመንገድ፣ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ መሰረተ ልማት የተሟላላቸው ናቸው።

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በ2009 በጀት ዓመት 18 ሺህ 496 የ40/60 ፕሮግራም ቤቶችን እንደሚያስተላልፍ ቢገልፅም እስካሁን የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት እጣ አልወጣም-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።