32 የአሻባሪው ህውሃት ተላላኪዎች በቁጥጥር ሰር ዋሉ

ነሀሴ 11/2013 (ዋልታ) – የሽብርተኛውን ህወሃት ቡድን ጥፋት ለማስፈጸም ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሲገቡ የነበሩ 32 የጥፋት ተላላኪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አብልአዚም መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በቁጥጥር ስር የዋሉት በሽብርተኛው የህዋሃት አስተባባሪነት ከሃገር ውጭ ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱ ናቸው፡፡

ግለሰቦቹ በክልሉ ጠረፍ አካባቢ አሶሳ፣ ኩርሙክ ወረዳዎች በኩል ድንበር አቋርጠው ባለፉት ሶስት ተከታታይ ቀናት ወደ ክልሉ ሲገቡ መቆጣጠር መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት አብዛኞቹ ወጣቶች ሲሆኑ በሽብርተኛው ቡድን “የፌደራል መንግስት ተዳክሟል” በሚል የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ተታልለው ወደ ጥፋት መንገድ የገቡ ናቸው ብለዋል፡፡

እንዲሁም በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ሲሳተፍ የነበረው የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ቤህነን) ምክትል አመራር እና ፓርቲውን ወክለው በምርጫ የተሳተፉ እጩዎች፣ አሶሳ ከተማ ተቀምጦ ጥፋቱን ሲያስተባብር የነበረ የአሸባሪው አባል እንደሚገኙበት አብራርተዋል፡፡

የጥፋት ቡድኑ ተላላኪዎች የያዙት የጦር መሣሪያ፣ ቢላዋ፣ ገጅራ፣ ላፕቶፕ ካምፒዩተር፣ የባንክ ደብተር እና ሌሎችም ቁሳቁሶች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ግለሰቦቹን መቆጣጠር የተቻለው  በአካባቢው ማህበረሰብ ፣ሃገር መከላከያ እና ክልሉ ልዩ ሃይል እንዲሁም ሚኒሻ አባላት ጋር ባረጉት የተቀናጀ ጥረት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም አሸባሪው ህወሃት በክልሉ ያለምንም ካፒታል በግብርና ኢንቨስትመንት ስም ተሰማርቶ ከፍተኛ ገንዘብ ከልማት ባንክ ዘርፏል ያሉት ኮሚሽሩ በተለይ የክልሉን ወርቅ ሃብት በህገ-ወጥ መንገድ ማጋበሱን አስታውሰዋል፡፡

ከለውጡ በኋላ የክልሉ ህዝቦች በተለይም ወጣቱ በስፋት ተደራጅቶ የተፈጥሮ ማዕድኑን በማልማት ኑሮውን መቀየር መጀመሩን ጠቁመው ይህ ለአሸባሪው  ህወሃት እንዳልተመቸው አስረድተዋል፡፡

በሽብር ቡድኑ የጥፋት ሴራ በተለይ  የኢትዮጵያ ህዝብ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ በሚመጣበት ማንኛውም ጫና እንደማይደራደር የገለጹት ኮሚሽሩ የክልሉ ህዝብ የጥፋት ተላላኪዎችን አሳልፎ የሰጠው ይህንኑ አቋም በመያዝ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

ክልሉ  ከፌደራል የጸጥታ ሃይሎች በመቀናጀት የጥፋት ቡድኑ ሃገር የማፍረስ እቅድ አስቀድሞ ማክሸፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮሚሽነር አብዱልአዚም ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ህብረተሰቡም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም  ጠይቀዋል፡፡