መንግስት የደቡብና የኦሮሚያ ክልሎች 3 ዞኖች ተፈናቃዮችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ እየሰራ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር

በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞን አጎራባች አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን ቀድሞ ወደ ነበሩበት ለመመለስ መንግስት እየሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስታውቋል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ  የተመራ ቡድን ትላንት ተፈናቃዮችን ከጎበኘ በኋላ በተካሄደ ውይይት ላይ እንዳሉት በነዚህ አካባቢዎች በደረሰው ጉዳትን በተመለከተ  ከሳምንት በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ውይይት ተደርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በአፋጣኝ እርቅ ወርዶ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀድሞ ስፍራቸው ለመመለስ የሚያስችል አቅጣጫ መቀመጡንም ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ ክልሎች የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት አባገዳዎችና የጸጥታ ሀይሎችን በማቀናጀት በሚከናወነው ወደ መኖሪያቸው የመመለስ ስራ ዙሪያ ዳግም ውስብስብ ችግር እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ሁሉም ቤቱን መፈተሽ እንዳለበት ጠቁመው ስሜት የሚኮረኩር ነገር በማድረግ ከመካሰስ በመራቅ ሁሉም የመፍትሄው አካል በመሆን ከአባገዳዎች ጋር በመሆን የተጀመረውን ˝የጎንዶሮ˝ ስርዓት ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ይህን ጉዳይ የሚከታተል ብሄራዊ ኮሚቴ መሰየሙንና ማን ምን ይሰራል የሚለው በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርና በተሰየመው ብሄራዊ ኮሚቴ እቅድ ወጥቶ በሁለቱ ክልሎችም ተመሳሳይ ኮሚቴ መዋቀሩን ገልጸዋል፡፡

ጊዜው የመኸር ወቅት በመሆኑም እንዳይባክን ችግሩን በፍጥነት መፍታት አስፈላጊ መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ በበኩላቸው የጠፋውን የሰው ህይወት መመለስ ባይቻልም የወደመውን ንብረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን መተካት እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስትም ተፈናቃዮች እስኪቋቋሙ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው ሁለቱ ክልሎች ሰላምን የሚያውኩና የሚያፈናቅሉ አካላትን ለህግ ለማቅረብ በትኩረት እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ እንዳሉት  ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ሜዳ ላይ ያለው ህብረተሰብ መጠለያ ማግኘት የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ቀጥሎም ወደ ነበሩበት ስፍራ መመለስ ነው።

“ይህ የተፈናቀለ ህዝብ የኦሮሚያ ሰው ነው ማንም ከየትኛውም አካባቢ ኢትዮጵያዊያንን የማሳደድና የማፈናቅል መብት የለውም ኢትዮጵያ የሁላችንም ሀገር ናት ይህን የሚያደርገውን አካል ህጋዊ እርምጃ በመተባበርና በአንድነት መውሰድ አለብን” ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን የሰውን ህይወት ለመታደግና አሁን የእርሻ ጊዜ በመሆኑም በፍጥነት ወደ ቀያቸው ለመመለስ የህዝብ አመራሮች የሀይማኖት አባቶች አባገዳዎች በትኩረት እንዲሰሩ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ከሁለቱ ክልሎችና ከፌዴራል መንግስት የተወጣጡ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡ (ኢዜአ)