በክረምት ትምህርት መርሐግብር ከ45 ሺህ በላይ የትምህርት ባለሙያዎች ስልጠና ይገባሉ

በያዝነው የክረምት ትምህርት መርኃግብር ከ45 ሺህ በላይ መምህራን፣ ርዕሰ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች ስልጠና እንደሚጀምሩ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የትምህርት አመራር  ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ አሰፋሽ ተካልኝ እንደገለጹት የክልሎችን የስልጠና ፍላጎት ጥያቄና የዩንቨርስቲዎችን የቅበላ አቅም በማጣጣም የስልጠና መርሃ ግብሩን ለመጀመር ዝግጅቱ ተጠናቋል።

የክረምት መርሃ ግብሩ በአገር አቀፍ ደረጃ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ለመምህራን፣ ርዕሰ መምህራንና ለሱፐር ቫይዘሮች የሚሰጡት የትምህርት ፕሮግራሞች በቀጣዩ ሳምንት እንደሚጀመሩ ገልጸዋል።

የስልጠና መርሃ ግብሩ የትምህርት ጥራትን እንዲያስጠብቅ የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱ ላይ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ አክለዋል።

የመምህራን ብቃት ማሳደግ ለትምህርት ጥራት ትልቅ ግብዓት በመሆኑ የመምህራን የስራ ላይ እና የቅድመ ስራ ስልጠናዎች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የስልጠናዎቹ አላማም የአጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ  የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅና ለአገሪቷ ልማት ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ዜጎችን ማፍራት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በክልሎች የኮሌጅ መምህራንን የትምህርት ደረጃ  ወጥና ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ መመሪያው በመሻሻል ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

መመሪያው በኮሌጆቹ ማሟላት ያለባቸውን የመጀመሪያ፣ የሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ መምህራንን ቁጥር ያካተተ መሆኑንም አክለዋል። (ኢዜአ)