የጂማ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ሙያተኞች የትርፍ ሰዓት ክፍያ ዘገየብን ሲሉ ቅሬታቸውን ገለጹ

የጂማ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ሙያተኞች የትርፍ ሰዓት ክፍያ ሳይፈጸም ከአራት ወራት በላይ በማስቆጠሩ የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸዋል፡፡

በሆስፒታሉ የላቦራቶሪ ቴክኖሎጂስትና ነርስ ሚኪያስ  ጋሻው እና ሽፈራው በርሲሳ  ለዋልታ ቴሌቪዥን እንደገለጹት ሆስፒታሉ የመደበኛ እና የትርፍ ሰዓት ክፍያን ጨምሮ መክፈል ባለመቻሉ በስራቸው ላይ ጫና ፈጥሮባቸዋል፡፡

በሆስፒታሉ ባለሙያች በአግባቡ ስለማይያዙ በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን የሚለቁ ባለሙያዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡

በጂማ ከተማ ውስጥ በሚገኙ በፈዴራል እና በክልል በሚተዳደሩ ሆስፒታሎች መካከል ያለው የደመወዝ ልዩነት ባለሙያዎችን ለቅሬታ የዳረገ ሌላኛው ምክንያት መሆኑ  ተጠቅሷል።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ኢሳያስ ከበደ በበኩላቸው የባለሙያዎቹ ቅሬታ አግባብ እንደሆነ ጠቅሰው ሆስፒታሉ በገጠመው የበጀት እጥረት  ሳቢያ ተገቢውን ክፍያ ለመፈጸም እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነ ያመለከቱት ዶክተር ኢሳያስ የደመወዝ ልዩነትን የተመለከተ ቅሬታ በፌዴራል ደረጃ የሚመለስ በመሆኑ ቅሬታውን አቅርበን ምላሹን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡