የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀገር ውስጥና የውጭ ሲኖዶሶች በአንድ ሲኖዶስ ለመመራት ተስማሙ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሁለቱ ሲኖዶስ የነበረው ልዩነት በዕርቀ ሰላም ወደ አንድነት ተመለሰ።

ባለፉት 27 ዓመት በሁለት ሲኖዶስ ስትመራ የቆየችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ወደ አንድ ለማምጣት የሰላምና የእርቅ ጉባዔው በዋሸንግተን ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርዔል ቤተክርስቲያን ባለፈው እሁድ የሁለቱም ልኡካን አባቶች በተገኙበት የጋራ ፀሎትና የመክፈቻ መርሐ ግብር ተጀምሯል።

ሲኖዶሶቹ ለሁለት በመከፈላቸው ምክንያት ችግር ላይ የነበሩ የእምነቱን ተከታዮች ወደ አንድነት ለማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ውይይት በማድረግ ወደ አንድነት እንደተመለሱ ተመልክቷል።

በእስካሁኑ ውይይታቸው በአንድ ሲኖዶስ ለመመራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ነው የተነገረው።

በተጨማሪም "የሀገር ቤት ሲኖዶስ" እና "ስደተኛ ሲኖዶስ" የሚባለውን ለማስቀረት ተስማምተዋል።

ይህ የሰላምና የእርቅ ጉባኤ እስከ አርብ ድረስ የሚቆይ እንደሆነና በውይይቱ መጨረሻ መግለጫ እንደሚሰጥ ነው የገለፁት።

በቅርቡ ወደ አሜሪካ ያቀኑትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አሸማጋይ ኮሚቴ አባላትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በፅህፈት ቤታቸው ማነጋገራቸው የሚታወስ ነው።

በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የአስታራቂ ኮሚቴ አባላቱ በእርቅና ሰላም ረገድ አርዓያ መሆን እንዳለባቸው በመጥቀስ፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሰላም የሀገር ሰላም እንደሆነ ተናግረዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ የጠፋውን ሰላም ወደ ነበርበት እንዲመለስ ለማድረግም 2003 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ከዚህ በፊት ማስታወቀቸው ይታወሳል።

2010 ዓም ጥቅምት ወር የቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔን ተከትሎ በራሱ ተነሳሽነት ከካህናትና ምእመናን የተወጣጣ የሰላም ኮሚቴ ያቀረበውን የእርቅ ጥያቄ ተቀብሏል።(ኤፍ..)