ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አዲስ አበባ ገቡ

አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አዲስ አበባ ገቡ።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በእምነቱ አባቶች፣ በጳጳሳት፣ በካህናት እንዲሁም በእምነቱ ተከታዮች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ዘማሪያንና ዲያቆናት አቡነ መርቆርዮስንና ብጹአን አባቶችን በከበሮና በበገና በታጀበ መንፈሳዊ ዝማሬ ተቀብለዋቸዋል።

እንዲሁም በአቀባበል ስነስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ መሐመድ አሚን ጀማል፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ እና የሌሎችም የእምነት አባቶች ተገኝተዋል፡፡

ባለፉት 26 ዓመታት ለሁለት ተከፍለው የሀገር ቤትና የውጭ ሲኖዶስ እየተባለ ሲጠሩ የነበሩት ሁለቱ ሲኖዶሶች ቃለ ውግዘታቸውን አንስተው ሰሞኑን ወደ ዕርቅ መምጣታቸው ይታወሳል፡፡

ዕርቀ ሰላሙን ተከትሎ አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ እና ብፁአን አባቶች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጋር አዲስ አበባ ገብተዋል።

ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ እስከ መንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ድረስ የቤተ ክርስቲያኗን ቀኖና በጠበቀ መልኩ የአቀባበል ስነ ስርዓት እየተከናወነ ይገኛል።

የሀገር ውስጡ ቅዱስ ሲኖዶስ ከሦስት ቀናት በፊት በውጭ ሲኖዶስ ላይ አሳልፏቸው የነበሩ የ1984፣ 1985 እና 1999 ዓመተ ምህረት ውግዘቶችን ማንሳቱ የሚታወስ ነው።

በተመሳሳይ በውጭ ሀገር የሚገኘው ሲኖዶስ ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ በሚገኘው ሲኖዶስ ላይ አሳልፏቸው የነበሩ ቃለ ውግዘቶችን ባለፈው ሳምንት ማንሳቱ ይታወቃል።

ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአንድ የቅዱስ ሲኖዶስ አመራር እንድትመራም ተወስኗል።

በስምምነቱ መሰረትም ሁለቱ ቅዱሳን ፓትርያርኮች በሕይወት እስካሉ ድረስ ቤተ ክርስቲያቲያኗን በእኩልነት የአባትነት ክብራቸውን ጠብቃ እንደምትይዝ ተነግሯል።

የፊታችን ቅዳሜ ሐምሌ 28 በሚሊኒየም አዳራሽ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ምዕመናን በጥቅሉ ከ30 ሺህ ሰው በላይ በሚገኝበት ሁለተኛው የዕርቀ ሰላም ፕሮግራም መዘጋጀቱም ተገልጿል።

በዚህ እርቀ ሰላም መሰረት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በሕገ ቤተክርስቲያን መሠረት የአስተዳደር ስራን ሲሰሩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ደግሞ በጸሎት እና በቡራኬ ቤተክርስቲያኗን እንዲመሩ ይደረጋል ነው (ኤፍቢሲ)