የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ አንድነትን ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል

አራተኛው ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውንና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ አንድነትን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን  በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነመርቆሪዮስ በስደት ከነበሩበት ሰሜን አሜሪካ ወደ መንበራቸው መመለሳቸውን ቢቢሲና አናዱሉ ዘግበውታል፡፡

አቡነመርቆሪዮስ ከ27 አመታት የስደት ቆይታ በኋላ አዲስ አበባ መግባታቸውንና ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው በስፋት ተዘግቧል፡፤

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ አሜሪካ ማቅናታቸውን ተከትሎ ተከፋፈሎ የነበረውን የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ለማግባባት ባደረጉት ጥረት የተገኘ ስኬት ስለመሆኑ ቢቢሲ በመረጃ አስፍሯል፡፡

ቤተ ክሪስቲያኗ የኮሚኒስታዊው  ስርዓት ገዥ የነበሩት አቶ መንግስቱ ሀይለማሪያም በ1983 ዓ.ም ከስልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ ለሁለት ተከፈላ እንደነበር አስታውሷል፡፡

በመሆኑም አቡነመርቆሪዮስ  ሀይማኖታዊ ቡራኬ በመስጠት የሚያገለግሉ ሲሆን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ደግሞ አስተዳደራዊ ሁነቶችን አንደሚመሩ መወሰኑን አስፍሯል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ከአራተኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ መሰረት እንዳላትና ቤተክርስቲያኗም ቀደምት ስለመሆኗ የቢቢሲ ጽሁፍ ያተተ ሲሆን ከ1950 ዎቹ አንስቶ ከግብፅ የሚደረግላትን የጳጳስ ሹመት መቅረት ተከትሎ አቡነ መርቆሪዮስ አራተኛው ጳጳስ ስለመሆናቸው አስፍሯል፡፤

 

ከሀገር መውጣታቸውን ተከትሎም አቡነ ጳውሎስ አምስተኛ ፓትሪያርክ ሆነው  መሾማቸውን አያይዞ ያነሳው ዘገባው፤ ኢትዮጵያ በዓለማችን የጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናትና ቅርስ ባለቤት ስለመሆኗ በስፋት አስነብቧል፡፡

 

የቱርክ መገናኛ ብዙሃን የሆነው አናዱሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ፓትሪያርክ አቡነመርቆሪዮስ ከ27 አመታት ስደት በኋላ ለሀገራቸው ምድር መብቃታቸውን በፊት ገፁ አሰፍሯል፡፡

ወደ መዲናዋ አዲስ አበባ ሲገቡም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የተመራ ከፍተኛ የባለስልጣናት ለኡክ  አጅቧቸው እንደነበረም አስነብቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውንንና ትውልደ ኢትዮጵያውን በሀገራቸው ፖለቲካና ኢኮኖሚ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ለማቅረብ ወደ ስፍራው ማቅናታቸውን አስታውሶ፤ ቆይታቸው ፍሬያማ አንደነበርና የሲኖዶሱ አንድነት ሁነኛ ማሳያ ስለመሆኑ ገልጧል፡፡