ሆስፒታሉ የቤትለቤት የቲቢ ምርመራና ሕክምና አገልግሎት በይፋ ጀመረ

የቅዱስ ዼጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቲቢ ሕሙማንን ቁጥር ለመቀነስ ብሎም ከሀገሪቱ ለማጥፋት ያረዳል ያለውን የቤትለቤት የቲቢ ምርመራና ሕክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውቋል።

የቅዱስ ዼጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ኃላፊ አቶ ያዕቆብ ሰማን ኢትዮዽያ ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት በመስጠት በምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ውስጥ አካትታ እየሰራች እንደሆነና የቤት ለቤት ምርመራው የዚሁ አካል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ህብረተሰቡ በሽታው ቶሎ ህክምናው ከተወሰደ መዳን የሚችል መሆኑን አውቆ እራሱን እንዲጠብቅና የህክምና ምርመራ እንዲያደርግ ኃላፊው አሳስበዋል፡፡

የቤት ለቤት ምርመራና ህክምናው ከዕድሮች ጋር በመቀናጀት የሚሰራ ሲሆን ሰዎች ተጠጋግተው በሚኖሩባቸው አካባቢዎች፣ በህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች አንዲሁም በብዛት ህብረተሰቡ በሚገለገልባቸው መስሪያ ቤቶችን እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡

ኢትዮዽያ በአለም ከፍተኛ የቲቢ ስርጭት ካለባቸው 30 ሀገሮች ውስጥ አንዷ ስትሆን በሀገሪቱ ከአንድ መቶ ሺህ ሰዎች አንድ መቶ ስምንቱ የቲቢ ሕመምተኞች ናቸው።