የቦሌ ክፍለ ከተማ የልማት ተነሺዎች ተለዋጭ ቦታ ባለማግኘት መጉላላታቸውን ገለጹ

በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 በተለምዶ ወጂ ስላሴ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩ የልማት ተነሺዎች ተለዋጭ ቦታ ባለማግኘታቸው መጉላላታቸውን ገለጹ፡፡  

"የምትኖሩበት ቦታ ለልማት ስለሚፈለግ በምትኩ ሌላ ይሰጣችኋል ተብለን ከቦታው ብንነሳም ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ምንም አይነት መፍትሄ አልተሰጠንም" ሲሉ ነዋሪዎቹ ለዋልታ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ቦታውን ለ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት ግንባታ  ለማዋል ሲባል የ271 አባወራዎች መኖሪያ ቤት እንደፈረሰባቸው ተናግረዋል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽመልስ ዘውዴ ለነዋሪዎቹ ቦታ የአየር ካርታ ባለመኖሩ ሌላ ተለዋጭ ቦታ ለመስጠት መመሪያው እንደማይፈቅድና ለጉዳያቸው መፍትሔ መስጠት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ታምራት አስናቀ በበኩላቸው ቅሬታ አቅራቢዎች መመሪያውን ስለማያሟሉ ተለዋጭ ቦታ እንዳልተሰጣቸው ገልጸው በክፍለ ከተማው ከ600 በላይ የቀበሌ ቤቶች እየተገነቡ በመሆኑ ግንባታው ሲጠናቀቅ እንደየችግራቸው ክብደት የሚስተናገዱ ይሆናል ብለዋል።

ለጥያቄያቸው መፍትሄ ለማግኘት እስከ ተወካዮች ምክር ቤት የሄዱ መሆናቸውንና ምንም አይነት መፍትሄ ባለመሰጠቱ ለችግር መጋለጣቸውንና መንግስት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡