በመንገድ የሚጣሉ ደረቅ ቆሻሻዎች የፈሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን እየዘጉ መሆናቸውን የከተማዋ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የሚያስወግዷቸው ደረቅ ቆሻሻዎች ያላግባብ መንገዶች ላይ የሚጣሉ በመሆናቸው የፈሳሽ ማስወገጃ ቦይና ቱቦዎችን እየዘጉ በመሆኑ ጥንቃቄ እንዲደረግ  የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አሳስቧል፡፡

ከተለያዩ መኖሪያ ቤቶች የሚወጡ ደረቅ ቆሻሻዎችና ወደ ቱቦ መግባት የማይገባቸውን ቁሳቁሶች ህብረተሰቡ ኃላፊነት በጎደለው ስሜት እያስወገደ መሆኑን የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጥኡማይ ወልደገብሬኤል ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

ይህም በከተማዋ ውስጥ ያሉ የፈሳሽ ማስወገጃ ቱቦችን በመዝጋት በተለይ አሁን እየጣለ ካለው ዝናብ ጋር ተያይዘው ቱቦዎች እንደፈነዱ እና የተለያዩ የከተማዋ አስፓልቶች በጎርፍ እንድጥለቀለቁ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ወደ ግለሰቦች ቤት በመግባት የጎርፍ መጥለቅለቅ እያስከተለ መሆኑን አቶ ጥኡማይ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኤሌክትሪክ መስመሮችን ኃላፊነት በጎደለው ስሜት በፈሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ውስጥ ያለባለስልጣኑ ዕውቅና መዘርጋቱ በየቦታው ችግር እያስከተለ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከተለያዩ የመንግስት ሴክተርሮች ጋር በቅንጅት ያለመስራት ችግርም መንገዶችን አስቸጋሪ ከሚያደርጉ ድርጊቶች ይጠቀሳሉ ብሏል፡፡