693 የህግ ታራሚዎች በይቅርታና በምህረት ተፈቱ

693 የህግ ታራሚዎች በይቅርታና በምህረት መፈታታቸውን የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አስታወቀ።

አስተዳደሩ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ታራሚዎች የጸደቀውን የምህረት አዋጅ መነሻ በማድረግ ሲፈቱ የመጀመርያው ነው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1096/2010 የምህረት አዋጅን ማጽደቁ ይታወሳል።

ዛሬ የተለቀቁት ታራሚዎችም በአዋጁ አንቀጽ 5 ሥር በተዘረዘሩ በህገ-መንግስቱ ስርዓት ላይ የሚደረግ ወንጀል፣ የህገ-መንግስታዊ ስልጣንን ተግባራዊነት ማሰናከል፣ የጦር መሳሪያ ይዞ በማመጽ የእርስ በእርስ ጦርነት ማስነሳት፣ የአገር ክህደት ወንጀል፣ የስለላ ወንጀል፣ የአገር መከላከያ ኃይልን መጉዳት በሚል በተዘረዘሩ ወንጀሎች የተከሰሱ ነበሩ።

በቀጠሮ ላይ የሚገኙ 63 የቀጠሮ እስረኞችና 146 የተፈረደባቸው በድምሩ 209 የህግ ታራሚዎች በምህረት አዋጅ ህጉ መሰረት ዛሬ እንዲለቀቁ መደረጉን ነው አስተዳደሩ ያስታወቀው።

በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ባሳዩት መልካም ባህሪ በተለያዩ የወንጀል አይነቶች የተከሰሱና በፍርድ ቤት ውሳኔ ጥፋተኛ ተብለው የተፈረደባቸው የህግ ታራሚዎችና የቀጠሮ እስረኞች በይቅርታ አዋጅ ቁጥር 840/2006 መሰረት ለ484 የህግ ታራሚዎች መንግሥት ይቅርታ በማድረጉ ከማረሚያ ቤት እንዲወጡ ተደርጓል።

አስተዳደሩ በመግለጫው እንዳመለከተው በአጠቃላይ 693 የህግ ታራሚዎች በምህረትና በይቅርታ ከማረሚያ ቤት ወጥተዋል።

ከዚህ በፊት የህግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው በሚያሳዩት መልካም ባህሪ በተለያዩ ጊዜያት ከማረሚያ ቤት ወጥተው ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ መቆየታቸውን ያስታወሰው መግለጫው የምህረት አዋጁ ከጸደቀ በኋላ መንግስት ለታራሚዎች ይቅርታ ሲያደርግ ይህ የመጀመርያው መሆኑን ጠቁሟል።

ኅብረተሰቡ የተለቀቁ ታራሚዎችን ተቀብሎ እንደማንኛውም ዜጋ ተገቢውን ክብር በመስጠት በተለያዩ ሥራዎች እንዲሰማሩ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግም ነው የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ጥሪ ያቀረበው።

የህግ ታራሚዎቹም ወደ ኅብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ያዳበሩትን መልካም ባህሪ የበለጠ በማጠናከርና ራሳቸውን ከወንጀል በማራቅ የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ በመደገፍ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቋል። (ኢዜአ)