ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለመክፈት ስምምነት ፈጸመ

ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት  የተሰኘ ዓለም ዓቀፍ የበየነ-መንግስታት ተቋም በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ  ጽህፈት ቤት ለመክፈት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ፡፡ 

ስምምነቱን የፈረሙት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እና የተቋሙ የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ  ስራአስኪያጅ  ዴክሲፖስ አጉሪደስ ናቸው  ፡፡ 

ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ፣ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ቀርፃ ስራ ላይ በማዋል ተጨባጭ ውጤት በማስመዝገብ ዘላቂ ልማትና የአረንጓዴ ልማት የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ለዓለም ማሳየቷን የጽህፈት ቤቱ መከፈት ምስክር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተቋሙ የአፍሪካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መሆኗ ሀገሪቱ በአፍሪካ ደረጃ እንዲሁም በዓለምአቀፍ መድረኮች ለአረንጓዴ ልማት የነበራትን የመሪነት ሚና እንደሚያጎላውም ተናግረዋል፡፡ 

ዴክሲፖስ አጉሪደስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የተቋሙ የአፍሪካ ጽህፈት ቤት እንድታስተናግድ የተመረጠችው በአፍሪካ ብሎም በዓለምአቀፍ ደረጃ የአረንጓዴ ልማት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆኗ ነው ብለዋል፡፡

 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ሀገሪቱ የጀመረችውን ዘላቂ ልማት በመደገፍ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት 27 ሀገራትን በአባልነት ያቀፈ ዋና መ/ቤቱን በደቡብ ኮሪያ ሴኦል ያደረገ የበየነ-መንግስታት ተቋም ሲሆን ኢትዮጵያ ከተቋሙ መስራች ሀገሮች መካከል አንዷ ናት፡፡