በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የጳጉሜ ፌስቲቫል ተካሄደ

በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የጳጉሜ  ፌስቲቫል በጉለሌ እፅዋት ማዕከል ተሂዷል

የፌስቲቫሉን መከፈት ያበሰሩትና የእለቱ የክብር እንግዳ የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው  እንደገለፁት ይህ የጳጉሜ ፌስቲቫል መጀመር በሀገራችን የኢኮ- ቱሪዝም እንዲስፋፋ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል፡፡

በተለይ በዚህ በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ፌስቲቫሉ መካሄዱ ተሳታፊዎች ስለ አረንጓዴ ልማት ጥቅም እንዲያውቁና ከዕፅዋት ጋር ያላቸው ቅርበት እንዲጎለብት ያደርጋል ብለዋል።

የፌስቲቫሉ አዘጋጅ ጳጉሜ አብ ፌስትቫል ሀላፊቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሀላፊ አቶ ሀይለአብ መረሳ እንደገለፁት የዚህ ፌስቲቫል መካሄድ ዋና አላማ ማህበረሰቡ ከአሮጌው አመት ወደ አዲሱ አመት ሲሸጋገር ይህን ተጨማሪ የጳጉሜ ቀናቶች በመዝናናት፤ባህልና ልምድ በመለዋወጥ እንዲሁም በጎ ተግባራትን እየሰሩ እንዲያሳልፉ በማሰብ ነው ብለዋል።

አቶ ኃይለአብ አያይዘውም ፌስቲቫሉ ከዚህ በተሻለ  በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲከበር የማድረግ ሠራዎች እየተሰራ መሆኑን ገልፀው ይህል ፌስቲቫል በአለም ላይ ካሉ ፌስቲቫሎች ተርታ በማድረስ ይበልጥ ሀገራችንን የምናስተዋውቅበት አጋጣሚ መፍጠር ይቻላል ብለዋል።

ፌስቲቫሉን  ለመታደም የመጡ የአፋር እና የአማራ ክልል የባህል የቡድን አባላት እንዲሁም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሠጡት አስተያየት ባህልን ከማስተዋወቅና የህዝብ ለህዝብ ትስስር በመፍጠሩ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል ።

በፌስቲቫሉ የተለያዩ ዝግጅቶች የቀረቡ ሲሆን  እስከ ጳጉሜ አራት ዝግጅቱ የሚቀጥል ሲሆን ፌስቲቫሉን  በአለም አቀፍ ደረጃ ለማሳወቅ እየተሰራ መሆኑን ታውቋል።