ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ በኮፊ አናን የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ለመገኘት ወደ ጋና አቀኑ

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ ለመገኘት ወደ ጋና ማምራታቸው ተነገረ፡፡

የኮፊ አናን የቀብር ስነስርዓት በነገው ዕለት በጋና መዲና አክራ ይፈጸማል ተብሏል፡፡

በቀብር ስነስርዓቱ ላይም የተለያዩ ሀገራት መሪዎችና የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች አክራ ገብተዋል፡፡

ከሁለት ቀናት በፊት በተመድ ሰንደቅ አላማ የተሸፈነው የአናን አስከሬን ጋና ኮቶካ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ሲደርስ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት በቦታው በመገኘት ተቀብለዋል፡፡

የሀገሪቱ መዲና ፖሊስም ለሦስት ቀናት ያህል ዝግ የሚሆኑ ሁለት አውራ ጎዳናዎችን ይፋ አድርጓል፡፡

ኮፊ አናን ለአጭር ጊዜ ባጋጠማቸው ህመም ከ27 ቀናት በፊት በስዊዘርላንድ በ80 ዓመታቸው ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡(ኤፍ.ቢ.ሲ)