የሀገር ሽማግሌዎችና ባለድርሻ አካላት ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸውን ወገኖች የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በቡራዩ እና ኦሮሚያ ልዩ ዞን አካባቢ በተፈጠረው ግጭት ተፈናቅለው በመድኃኒዓለም መሰናዶ ትምህርት ቤት ለተጠለሉ ተፈናቃዮች ድጋፍ ተደረገ።

የጋሞ ጎፋ ዞን የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በዛሬው ዕለት በቡራዩና አካባቢው ጉዳት ለደረሰባቸውን ወገኖች የሚውል  የአምስት ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በጉብኝቱ ተሳታፊ የሆኑት የጋሞ ጎፋ  ምሁር  ዶክተር ቶራ አበበ  እንደገለጹት ዛሬ ባዩት ነገር እጅግ ማዘናቸውንና ይሆናል ብለው ያላሰቡት ነገር ሆነው በማግኘታቸው ጥልቅ የሆነ ሀዘን እንደተሰማቸው በመግለጽ በቀጣይ መሰል ድርጊት እንዳይፈጸም ከመንግስት ጎን በመሆን እንሰራለን ብለዋል፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አንጀሎ አርሼበበኩላቸው  የዞኑ ህዝብ ሥራ ወዳድ እና ከሌላው ዜጋ ጋር ተዋዶ መኖር የሚችል ህዝብ ሆኖ ሳለ አሁን ላይ የሆነው ነገር ተገቢ ባይሆንም አንዴ ሆኗልና የጋሞ ጎፋ ህዝብ ይቅር ባይ በመሆኑ ይቅርታ በማድረግ የበቀል ጥፋት እንዳይፈጸም ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ ተጎጂዎቹን ለመደገፍ እና ወደ ቀድሞ ኑሯቸው እንዲመለሱ ለማስቻል አሁን ከተደረገው የ5 ሚሊዮን ብር ባለፈ በቀጣይም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡  

ከጎብኚዎች ጋር የተገኙት የጋሞ ጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ ለተጎጂዎቹ ከዚህ በኋላ ማልቀስ እንደማያስፈልግና ከጎናቸው በመሆን ድጋፋቸው እንደማይለይ ገልጸው በዚህ ድርጊት የተሳተፉ አካላትንም ለፍትህ እንዲቆሙ ትግላችን እናደርጋለን ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ህብረተሰብ ለተጎጂዎቹ ላደረጉት ድጋፍና ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በጉብኝቱ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ከህዝቡ የተወጣጡ ተወካዮች፣ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች እና ምሁራን ተገኝተዋል፡፡