ከቡራዩና አካባቢው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀያቸው ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ከቡራዩና አካባቢው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀያቸው ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር ገለጸ፡፡

የቡራዩ ከተማ ከንቲባ አቶ ሰለሞን ፈዬ ጉዳት የደረሰባቸውን ቤቶች በመለየት አጥር የሌላቸውን በመጠገንና መስኮት የሌላቸውን በማስገባት ለመኖር አመቺ እንዲሆን በከተማዋ ሁሉም ቀበሌዎች እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡም በራሱ ተነሳሽነት ከፀጥታ አካላት ጋር ወንጀለኞችን ለማጋለጥ እየሰራ መሆኑንና በቀጣይም መንግስት የህግ በላይነትን እንደሚያረጋግጥም ከተማ አስተዳደሩ ገልጸዋል፡፡

ሰሞኑን በቡራዩ ከተማ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የተፈናቀሉ ዜጎች ከሁለቱም ወገኖች ከተወጣጡ የሃገር ሽማግሌዎች በመመራት ቀያቸውን ጎብኝተዋል፡፡

መስከረም 11 ቀን 2011 ዓ.ም 25 አባወራዎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሃብት ንብረታቸውን ከጎበኙ በኃላ መንግስት እና ህብረተሰቡ በጋራ የጀመሩትን የአካባቢውን ጸጥታ እንዲያስከብሩ ጠይቀዋል፡፡

በቅርቡም ወደ ቀያቸው መመለስ እንደሚፈልጉ የገለጹት ተፈናቃዮች በአካባቢው ለአመታት የኖሩ በመሆኑ የተፈጠረውን ተግባር እንደሚያወግዙ ገልጸዋል፡፡