የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።

ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በመልክታቸው፥ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ ለሚሠጠው የኢሬቻ በዓል እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

ዘንድሮ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል በተቀናጀ እና አስገራሚ በሆነ መልኩ እንዲከበር ሁሉም የህብረተሰብ አካላት የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አስተላልፈዋል።

አባ ገዳዎች፣ ወጣቶች እና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሙሉ ባህልን በሚያፅባርቅ መልኩ የኢሬቻን በዓል አንዲያከብሩም ጠይቀዋል።

የ2010 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል በተቀናጀ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተከበረ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ለማ፥ የዘንድሮውም ከአምናው በተሻለ መልኩ ሰላማዊ እና ባህላችንን ለዓለም በምናስተዋውቅበት መልኩ ሊከበር ይገባል ብለዋል።

የኢሬቻ በዓል የገዳ ሥርዓት ነፀብራቅ በመሆኑ ልክ እንደ ገዳ ሥርዓት ሁሉ የኢሬቻ በዓልንም በዩኔስኮ በዓለም ቅርሰነት ለማስመዝገብ እየተሠራ መሆኑን አቶ ለማ አንስተዋል።

ስለዚህ በዓሉን ለማክበር ወደ ስፍራው የሚሄዱ በሙሉ ከፖለቲካ ፓርቲ አርማ፣ ባንዲራ እና ዘፈኖች ራሳቸውን እንዲቆጥቡም ጠይቀዋል።

የዘንድሮ የኢሬቻ በዓል ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ መንግስት ከአባ ገዳዎች ህብረት እና ከወጣቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ አንስተዋል።

ከጤና ጋር ተያይዞ ችግር ካጋጠመም የጤና ባለሙያዎች ከወዲሁ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን መግለፃቸውን ከኦሮሚያ ክለል የመንግሰት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)