የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምደባ ይፋ ሆነ

የመንግሥት ከፍተኛ ትምህረት ተቋማት ምደባ በዛሬው ዕለት  ይፋ ማድረጉን አገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ ።

ኤጀንሲው የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤትን ከገለጸ ጀምሮ ለምደባው የሚረዱ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲያካሄድ መቆየቱንና  ምደባውን  በዛሬው ዕለት ከ 8 ሰዓት ጀምሮ ለተማሪዎች ይፋ  ማድረጉ ተገልጿል ። 

ባለፈው ዓመት ከግንቦት 27-30 ድረስ በተሠጠው የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና 154,010 ወንዶች እንዲሁም 127,964 ሴቶች በድምሩ 281,974 ተማሪዎች ፈተናውን የወሰዱ ሲሆን በሐምሌ 24፣201 ውጤት ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡

ምደባው የተማሪዎችን ውጤት፣ የፊልድ እና የዩንቨርስቲ ምርጫ፣ የዩንቨርስቲዎችን የቅበላ አቅም፣ የወንዶችና የሴቶችን ምጥጥን ማዕከል ባደረገ እንዲሁም የልዩ ድጋፍ ተጠቃሚዎችንና  የጤና እክል ያለባቸው መሆኑን ማረጋገጫ ያቀረቡትን ተማሪዎች መሠረት በማድረግ ምደባውን ማከናወኑን ኤጀንሲው ለዋልታ ገልጿል ።

በዘንድሮው ዓመት  የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና የማለፊያ ነጥቡን አሟልተው ያለፉ 138,283 የሚሆኑ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች እንዲሁም 75,338 የሚሆኑ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ፤ በአጠቃላይ በድምሩ 213,621 ተማሪዎች  በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተመደቡ መሆኑን  ኤጀንሲው ገልጿል።

ከነዚህም መካከል 98,576 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች እና 51,229 የማህበራዊ ሳይንስ በድምሩ 149,805 ተማሪዎች በቅዱስ ጳውሎስ፣ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ባሉት 43 የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ይከታተላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዘንድሮ ዓመት በአጠቃላይ 95ሺህ 681 የተፈጥሮ ሳይንስና 51ሺህ 66 የማህበራዊ ሳይንስ  ተማሪዎች በድምሩ 146ሺህ 747 ተማሪዎች በ43ቱ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወይም ዩኒቨርስቲዎች መመደባቸውንም  ኤጀንሲ አስታውቋል ።

ኤጀንሲው ከላይ የተጠቀሱትን ማጣራቶችን ለማካሄድ ምደባውን በማዘግየቱ ምክንያት ቅሬታ  ሲያሰሙ ለነበሩ  ተማሪዎችና ቤተሰቦች ከወዲሁ ይቅርታ ጠይቋል ።

በተጨማሪም  ኤጀንሲው በዘንድሮ ዓመት በተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ ተቋማት የተመደቡ ተማሪዎች በምትሄዱበት የትምህርት ተቋማት የነገዋ ኢትዮጵያ በእናንተ  ትከሻ ላይ መሆኗን በመገንዘብ ለትምህርት ትኩረት በመሥጠት ለአገሪቱ እድገትና ልማት ላይ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ  የአደራ መልዕክት ተላልፏል ።

ተማሪዎች የተመደቡበትን የትምህርት ተቋም (ዩኒቨርስቲ) ለመመልከት  በኤጀንሲው ድረ-ገጽ app.neaea.gov.et በመግባት ማየት እንደሚችሉ  ኤጀንሲው ገልጿል ።