ባለፉት ዓመታት ታግዶ የነበረው የመካከለኛ ምስራቅ የሥራ ስምሪት ነገ እንደሚጀመር ተገለጸ

ላለፉት 5 ዓመታት ታግዶ የነበረው  የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት የስራ ስምሪት መስከረም 30 ቀን፤ 2011 ዓም በይፋ እንደሚጀመር የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ለዋልታ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፣ ውጭ አገር የሥራ ስምሪትን ለመጀመር የሚያስፈልጉት ቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመጠናቀቃቸው የውጭ አገር የስራ ስምሪቱ መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ/ም በሚካሄድ ስነ ስርአት በይፋ ይጀመራል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎች በአገራቸው ላይ ሰርተው መለወጥ እንዲችሉ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራ እየተተገበረ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ ውጭ ሃገር ሄደው የመሥራት ለሚፈልጉ ዜጎች ከዚህ በፊት በሥራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 104/90 እና አዋጅ ቁጥር 632/2001 አውጥቶ ሥራ ላይ አውሎ እንደነበር ይታወቃል፡፡

በስራ ላይ የነበረው አዋጅ ለሥራ ወደ ውጭ የሚሄዱ ዜጎች ተገቢው መብትና ክብራቸውን ከማስጠበቅ አኳያ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት የነበረበት ከመሆኑም በላይ ዜጎች ተገቢው  የክህሎት ስልጠና ሳያገኙ ይሄዱ ስለነበር በተቀባይ ሃገራት ገበያ ላይ ተወዳዳሪ መሆን እንዳልቻሉ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

 ከዚህም በተጨማሪ በአዋጁ ላይ የነበረው ክፍተት  ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር መንገድ በመክፈቱ በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲደርስም እንደቆየ ተገልጿል ፡፡

መንግስት ይህንን ጉዳይ በመመልከት የአሰራር ክፍተቱ እስኪስተካከል እና ደንብና ስርአት እስኪበጅለት ድረስ የውጭ ሃገር የስራ ስምሪት ከጥቅምት 14 ቀን 2006 ጀምሮ  እንዲታገድ ማድረጉ ይታወሳል ፡፡

በአሁኑ ወቅት ወደ ውጭ አገር በመሄድ ለመስራት ፍላጎት ያላቸውና መብታቸው፣ ደህንነታቸው እና ክብራቸው ተጠብቆ እንዲሠሩና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተደረገው ዝግጅት፣ መንግስት የውጭ አገር የሥራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008  በማውጣት ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡

የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአዋጁ ተግባራዊነትም በአገር ውስጥ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውቋል፡፡

በነገው ዕለት  የሚጀመረው  የውጭ  አገራት  ስምሪት መንግሥት የሁለትዮሽ ስምምነት በተፈራረመባቸው ሃገራት  በሆኑት ሳውዲ አረቢያ፣ ኳታር እና ጆርዳን እንደሆነመ በመግለጫው ተመልክቷል ።

በነገው ዕለት  በሚጀመረው  የስራ ስምሪት ይፋ ማድረጊያ ስነስርአት ላይ  የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ይገኛሉ ተብሎ  ይጠበቃል ።

የውጭ ሃገር የስራ ስምሪት ይፋ ማድረጊያ መርደኩ ላይም  ህብረተሰቡ ራሱን ከህገወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲጠብቅና  በተግባሩ ላይ ድርሻ ያላቸው አካላት ቅንጅታዊ አሠራሮችን  የሚያጠናከር አቅጣጫ እንደሚቀመጥም  ተጠቁሟል ።