ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከተፈናቀሉ ነዋሪዎች መካከል 40 ሺህ ያህሉ ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል- የኦሮሚያ ክልል መንግስት

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተፈናቀሉ 80 ሺህ ያህል ነዋሪዎች መካከል 40 ሺህ ያህሉ ወደ  ቀያቸው መመለሳቸውን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የማህበራዊ ዘርፍ ሃለፊ ወ/ሮ ጠይባ ሃሰን ገልጸዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተከሰው ግጭት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በነቀምት ከተማ የሚገኙ ሲሆን በአካባቢው ነዋሪዎች መንግስትና ሌሎች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች ድጋፍ እየተረደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

ተፋናቃዮችን በዚህ መንገድ በዘላቂነት ለማኖር የማይቻል መሆኑን የጠቆሙት ወ/ሮ ጠይባ  መንግስት ግጭቱ ተከስቶበት በነበረው አካባቢ የጸጥታውን ሁኔታ በዘላቂነት እንዲረጋጋ ለማድረግና ከሁለቱም ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ሙሉ በሙሉ ወደ  ቀያቸው ለመመለስ ትኩረት ተሰጥቶ አየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም በአብዛኛው ግጭቱ ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢወች መረጋጋት የተፈጠረ ሲሆን፥ በከማሽ ዞን አካባቢ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ገና የሚሰሩ ስራዎች መኖራቸውን ነው የተናገሩት።

የዚህ አካባቢ የሰላም ሁኔታ ሙሉ በሙሉ እስከሚረጋጋም ከአካባቢው የተፈናቀሉ ዜጎች በተጠለሉበት አካባቢ እንደሚቆዩም ገልጸዋል።

ኦሮሚያ ክልል በርካታ የሃገሪቱን ክልሎች እንደመዋሰኑ መጠን ከአሁን ቀደም ሲል በተለያዩ አካባቢዎች ችግሮች ይከሰቱ እንደነበረ ያስታወሱት ወ/ሮ ጠይባ ግጭቶች በአካባቢው ነዋሪዎች ይፈቱ እንደነበረም አስረድተዋል።

ወደፊትም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የማጠናከር ስራ  ተጠናክሮ  እንደሚቀጥልም የተገለጸ ሲሆን፥ ከዚሁ ጎን ለጎን ለግጭቱ መንስኤ የሆኑ አጥፊዎችን በመለየት የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ይሰራልም ነው ያሉት።

ነዋሪዎቹ በተፈናቀሉበት አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችም ተፈናቃዮቹ ወደቀያቸው አንዲመለሱ ጥያቄዎቻቸውን እያቀረቡ ነው ብለዋል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)