በአዲስ አበባ የውሃ አቅርቦትና ፍላጎቱ ያልተመጣጠነ በመሆኑ የውሃ ሥርጭቱን በፈረቃ ሊያደርግ መሆኑን ባለሥልጣኑ አስታወቀ

በአዲስ አበባ ከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ጋር ያልተመጣጠነ በመሆኑ የውሃ ሥርጭቱን  በጊዚያዊነት  በፈረቃ  ሊያደርግ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን  አስታወቀ ።

ባለሥልጣኑ በተለያዩ ምክንያቶች ካለው የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ጋር የተመጣጠነ ውሃ  ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ማቅረብ ባለመቻሉ በጊዜያዊነት የውሃ ሥርጭቱን በፈረቃ ለማድረግ ስለወሰነ  ስለሆነ ህበረተሰቡ ትብብሩን ያድርግልኝ ሲል ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ባለስልጣኑ በተለይ በከፍተኛ ደረጃ ውሃን የሚጠቀሙ ተቋማት የራሳቸውን ውሃ ቆፍረው እንዲጠቀሙ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

በአዲስ አበባ   በተፈጠረ  የውሃ እጥረት  በአብዛኛው አካባቢዎች አንድ ባለ ሃያ አምስት ሊትር ጀሪካን ወሃ ከሃያ ዓምስት ብር እስከ ሰባት አምስት ብር መሸጥ ተጀምሯል፡፡

የውሃ ችግሩ በአንዳንድ የአዲስ አበባ ሥፍራዎች ከአንድ ዓመት እስከ ሰባት ዓመት እንደ ቆየ ነዋሪዎቹ  ያስረዳሉ፡፡

ከቄራ  እስከ ጎፋ ማዞርያና አከባቢዎች  የዋልታ  ሪፖርተው  ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው  የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እንደሚገልጹት ለአንድ ዓመት ያህል ምንም አይነት ውሃ  እንዳልደረሳቸው አስተያየታቸውን ገልጸዋል ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በበኩሉ ለአንድ ዓመት ያህል ውሃ አልደረሰንም የሚለው የነዋሪዎች ቅሬታ መሠረት የለውም ብሏል፡፡

ሆኖም ባለሥልጣኑ በአገልግሎት አሠጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ሌሎች ችግሮችን እንደሚያውቃቸውና ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት እያደረገ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

የተቋሙ  አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች  የሚያሳዩዋቸውን የስነ ምግባር ችግሮችን ህብረተሰቡ በማጋለጥ እንዲተባበርም ጠይቋል፡፡