በአዲስ አበባ የማበረሰብ ጤና መድህን ስራን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ቢሮው አስታወቀ

በአዲስ አበባ ከተማ የማበረሰብ ጤና መድህን ስራን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የከተማው ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በቢሮው የማበረሰብ ጤና መድህን ስራ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢብራሂም ተካ ለዋልታ ቴሌቭዠን  እንደገለጹት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በከተማዋ 10 ወረዳዎች የማህበረሰብ ጤና መድህን ተደራሽ ለማድረግ  ሲሰራ መቆየቱን አውስተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በሰላሳ አምስት ተጨማሪ ወረዳዎች ላይ አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡

ቋሚ ደመወዝ የሌለውና የደሃ ደሃ የሆነ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሆነም አቶ ኢብራሂም ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች 350 ብር አመታዊ የአባልነት ክፍያ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ገደብ የለሽ የህክምና አገልግሎት እና መድሓኒት እንደሚያገኙም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የህክምና አገልግሎቱ የኩላሊት እጥበት፣ የካንሰር ህክምና እና የቀዶ ጥገና አገልግሎን እንድሚያካትትም ተገልጿል፡፡

በያዝነው ሳምንት የከተማው አስተዳደር በከተማዋ የሚገኙና በሺዎች የሚቆጠሩ የሴፍቲኔት ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች ይህንን አገልግሎት እንዲያገኙ ሙሉ ክፍያውን መሸፈኑንም አቶ ኢብራሂም አስረድተዋል፡፡