የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች በከተማዋ የሚገኘውን መስኪድና ቤተክርስቲያን በጋራ በመሆን አፀዱ

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች በከተማዋ የሚገኘውን መስጊድና ቤተክርስቲያን በጋራ በመሆን አፅድተዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከዚህ ቀደም የነበረውን የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና እምነቶች ተፈቃቅሮና ተቻችሎ በአንድነት የመኖር እሴትን ለማጠናከር የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ የአስተዳደሩ ወጣቶች ተናግረዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚስተዋሉትን ድርጊቶች ከተማዋ የምትታወቅበትን የሰላምና አብሮ የመኖር እሴት የማይገልፁ ነው ያሉት የከተማዋ ወጣቶች በጎ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነው ወጣት ሳዳም አባትና የክርስትና እምነት ተከታይ የሆነው ወጣት ቶማስ አይናለም በድሬዳዋ አስተዳደር ልዩ ስሙ ገንደቆሬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪዎች ሲሆኑ ከልጅነት ጀምሮ አብሮ ያደጉትና የተለያዩ ሀይማኖት ተከታይ ቢሆኑም የኃይማኖት ልዩነት በጓደኝነታቸው ላይ ተፅእኖ ሳይፈጥርባቸው መዝለቃቸውን ይገልፃሉ፡፡

ወጣቶቹም ይህ አብሮነታችን ሌሎችን የሚያስተምር ነው በማለት የገንደቆሬ መስኪድንና የሚካኤል ቤተክርስቲያንን በአንድነት አፅድተዋል፡፡

በጽዳት ላይ የተሳተፉ እነዚህ ወጣቶች የመቻቻልና አብሮ የመኖር እሴቶቻቸውን ለማበላሸት ለሚጥሩ አካላት አስተማሪ የሆነ ተግባር እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

የገንደቆሬ መስኪድ ኢማም ሼህ ሙሜ አብዱላሂ እና የደብረምህረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ቤተክሪስቲያን አስተዳዳሪ ሊቀብርሀናት ቀለመወርቅ ቢምረው ወጣቶቹ እምነትን ሳይለዩ ይህንን በጎ የሆነ ተግባር በማከናወናቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ድሬዳዋ አብሮ የመኖር የሰላምና የፍቅር ከተማ ለመሆኗ ማሳያ መሆኑንም የሀይማኖት አባቶቹ ገልጸዋል፡፡ (ምንጭ፤የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መ/ኮ/ቢሮ)