በበጀት ዓመቱ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካት ከፍተኛ ርብርብ እንደሚደረግ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር አስታወቀ

በዘንድሮ የበጀት ዓመት የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካት ከፍተኛ ርብርብ እንደሚደረግ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚንስትር ዶክተር አሚር አማን አስታወቁ፡፡

በመቐለ እየተካሄደ ባለው 20ኛው የጤና ዘርፍ አመታዊ ጉባኤ የተገኙት ዶክተር አሚር አማን  እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ የተጀመሩትን ሁሉም ፕሮግራሞች በማጠናከር  ለትራንስፎርሜሽኑ ስኬት በትኩረት ይሠራል ።

 በዚሁም በጤና ደረጃ የተጀመረውን የወረዳ ትራንስፎርሜሽን በማጠናከርና በማስፋት ሁሉን አቀፍ ትራንስፎርሜሽን እንዲኖርና ሀገራዊ ለውጡን በሚያፋጥን መልኩ እንዲተገበር ይደረጋል ብለዋል፡፡ 

የጤና አገልግሎቱ ፍትሃዊነትና ጥራት ለማረጋገጥ በቀጣይ ሁለት ዓመታት በመጀመሪያ ደረጃ የሚገኙ ሁሉም የጤና ተቋሞቻችን በሰው ሃይል፣ በውሃና መብራት፣ የሳኒቴሽን አገልግሎት፣ በህክምና መሳርያዎችና መድሃኒቶች እንዲሟሉላቸው እንደሚደረግ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ የተጀመረው የሆስፒታሎች ፈጣን ምላሽ አገልግሎት አሰጣጥ ወደ ሁሉም ክልሎች እንደሚስፋፋና በዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኙ ሆስፒታሎቻችን የአገልግሎት ጥራት እንዲሁም የግል ከፍተኛ ጤና ተቋማት በመጠቀም የስፔሻሊቲ ህክምና አገልግሎት እንዲስፋፋና እንዲጠናከር ይደረጋልም ብለዋል፡፡

ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎችና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የገለጹት ዶክተር አሚን የመደበኛ መረጃ ሥርዓትን የማዘመን ስራ በስፋት በማከናወን እንዲሁም የማህበረሰብ የጤና መረጃ ስርዓት በማጠናከር የመረጃ ሙልዑነት፣ ወቅታዊነትና ተአማኒነት ማሻሻል እንዲኖርና መረጃን ለውሳኔ አሰጣጥ የመጠቀም ባህላችንን ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ለዚሁም እንዲረዳ የአመራር ብቃትና አፈፃፀምን ለማጠናከር ልዩ ትኩረት ይሰጣል ብለዋል፡፡

የመድሃኒት አቅርቦቱ የተሟላና አስተማማኝ ለማድረግ የመድሃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ የማዘመን ስራ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የተጀመረው ሪፎርም የማጠናከር ስራ እንደሚሰራም ዶክተር አሚር አማን  ተናግረዋል  ። ( ምንጭ: ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር )