በጉብኝትና ንግድ ቪዛ ስም ወደ መካከለኛ ምስራቅ አገራት የሚደረገው ጉዞ ታገደ

በጉብኝትና በንግድ  ቪዛ  አማካኝነት ወደ መካከለኛ ምስራቅ አገራት የሚደረገው  ጉዞ  ከዛሬ ጀምሮ  መታገዱ ተገለጸ ፤

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ ኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ  ዋና መምሪያና  የፌደራል ፖሊስ በዛሬው ዕለት  በጋራ በሠጡት  መግለጫ  እንዳስታወቁት በጉብኝትና በንግድ ቪዛ ስም  ዜጎች  ወደ  መካከለኛው ምስራቅ አገራት  በመሄድ  ሞትን ጨምሮ ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸው በመረጋገጡ  ምክንያት ነው  ጉዞው እንዲታገድ የተደረገው ።

ዜጎች በጉብኝትና በንግድ ስም በሚገኙ ቪዛዎች ጉዞ በማድረግ የመካከለኛ ምስራቅ አገራት ከደረሱ በኋላም በህገ ወጥ  መልኩ  በሠራተኝነት እየተቀጡ  የተለያዩ ችግሮች ሲደርስባቸው  እንደሚታይ  በመግለጫው  ተገልጿል ።

እንደዚህ አይነት ህገ ወጥ ጉዞዎችንም  የሚፈጽሙት  ዋነኛ አካላቶችም  ህገ ወጥ ደላሎች ፣ በአስጎብኚነት ሥራ የተሠማሩ ድርጅቶችና  ህገ-ወጥ ኤጀንሲዎች መሆናቸው  በመግለጫው ተብራርቷል ።

በመካከለኛው ምስራቅ አገራት  በዜጎች ላይ  የሚደርሰውን  ችግር  ለመከላከልም  በአገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው  ህገ ወጥ የጉዞ አስወጋጅ ግብረ ኃይል ከዛሬ ጀምሮ  በሙሉ ኃይሉ ወደ ሥራ  መግባቱም በመግለጫው  በይፋ  ተገልጿል ።

በአገሪቱ  በህገ-ወጥ ጉዞ  ድርጊት ውስጥ  ያሉ አካላትና የጉዞ ሂደቱ ተሳታፊ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም  ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም  በመግለጫው ማሳሰቢያ ተሠጥቷል ።

ግብር ኃይሉ እንደገለጸውም ከሳውዲአረቢያ ፣ ኳታርና ጆርዳን  በስተቀር በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገራት  የሚደረገው ጉዞም  ህገ-ወጥ   እንደሆነም  በመግለጫው ተመልክቷል ።

በተለይም  የመገናኛ ብዙሃን ዜጎች  ህገ ወጥ ጉዞ  በማድረግ  ለእንግልትና ለተለያዩ ችግሮች እንዳይዳረጉ  አስፈላጊውን መረጃ  በመሥጠትና  ተከታታይ ይግንዛቤ ማስጨበጫ  ሥራዎችን በማከናወን ተገቢውን  ሚና እንዲጫወቱም በመግለጫው ጥሪ ቀርቧል ።