ለተፈናቀሉ ዜጎች እርዳታ የማድረሱ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል – ብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን

በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች አስፈላጊውን እርዳታ የማድረሱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዜጎች መፈናቀል በ2018 የመጀመሪያው አጋማሽ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

በዚህ ወቅት በግጭቶች ምክንያት በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 1 ነጥብ 4 ሚሊየን መድረሱንም መረጃው ያመላክታል።

የብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ ባለፉት ወራት በግጭቶች ምክንያት ብቻ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 1 ነጥብ 8 ሚሊየን መድረሱን ይገልጻል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ እንደገለጹት ዜጎች በዕለት ደራሽ የምግብ እርዳታ ድጋፍ እየተደረገላቸው ሲሆን፥ መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ስራ ለመስራትም የጉዳቱን መጠን እና ያን ለመተካት የሚያስፈልገውን አቅም የማጥናት ስራ ተጀምረዋል፡፡

ኮሚሽነር ምትኩ እንደሚሉት መንግስት እነዚህን ዜጎች ለመደገፍ ሙሉ አቅም አለው ቢባልም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር በጨመሩ ቁጥር ግን ለልማት የሚውለውን በጀት ይጎዳዋል።

ባለፈው ሳምንትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በፓርላማ ቀርበው በተፈጥሮ አደጋ እና በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ እየተሰራ ያለው ስራ እየተካሄዱ ባሉ የልማት ስራዎች ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑን አንስተው ነበር።

በተያዘው የፈረንጆቹ አመት ለተፈናቃይ ዜጎች 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገልጾ ነበር፤ ይህን ተከትሎም የመንግስታቱ ድርጅትን ጨምሮ አለም አቀፍ መንግስታዊ ድርጅቶች በራሳቸው መንገድ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አቶ ምትኩ ገልጸዋል።

ከአጠቃላይ ድጋፉ ውስጥም የውጭ ሀገር ድጋፍ ሰጪዎች ከ30 እስከ 40 በመቶውን እንደሚሸፍኑ የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፥ ተቋማቱ ያደረጉትን አጠቃላይ ድጋፍ ለማወቅ ግን ድጋፍ የሚያደርጉበት መንገድ ስለሚለያይ ጥናት ይፈልጋል ብለዋል።

እስከ ሰባ በመቶ የሚደርሰውን ድጋፍ የሚሸፍነው መንግስትም ባለው አቅም የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፥ ተጨማሪ ድጋፍ የሚያስፈልግ ከሆነ ደግሞ ከመጠባበቂያ በጀት ወጪ በማድረግ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት። (ኤፍ.ቢ.ሲ)