ለ7 ሚሊየን ህዝብ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሆስፒታል በባህርዳር ይመረቃል

ለ 7 ሚሊየን ህዝብ አገልግሎት መሥጠት የሚያስችል ሆስፒታል በባህር ዳር ከተማ በዛሬው ዕለት  ይመረቃል፡፡

‹‹ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል›› ተብሎ የተሰየመው ይህ ሆስፒታል 207 ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎበታል ተብሏል፡፡

በአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ  ግንባታው የተጀመረው ይህ ሆስፒታል፥ ከጥቅምት 2005 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መተላለፉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ ገልጸዋል፡፡

በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር በየቀኑ እስከ 2 ሺህ ህሙማንን የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን፥ ከ5 መቶ በላይ አልጋዎች እና 11 የቀዶ ህክምና መስጫ ክፍሎች እንዳሉትም ታውቋል፡፡

የቀዶ ህክምና መሥጫ ክፍሎችን ወደ 15 ለማሳደግም ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ማሟላት ያለበትን መስፈርት ያሟሉ ክፍሎች እንዳሉትም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ለሆስፒታሉ 51 ስፔሻሊስት ዶክተሮች እንደሚመደቡለትም ተነግሯል፡፡

አሁን ላይም 5 ሺህ የህክምና ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ያለው የመማሪያ ግቢ እየተጠናቀቀ መሆኑ ታውቋል፡፡

ለሆስፒታሉ በጀት እንዳልተመደበለት የተናገሩት የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው፥ ጉዳዩ በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ትኩረት እንዲሠጠው ጥሪ አቅርበዋል፡፡  (ምንጭ: የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት)